መቻል የበርካታ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

ከቀናቶች በፊት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለው የነበሩት መቻሎች የተጨማሪ ስምንት ተጫዋቾች ዝውውርን አጠናቀዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተካፋይ የሆነው እና ያለፉትን አራት ዓመታት በአሰልጣኝ ስለሺ ገመቹ እየተመራ ያለው መቻል ከቀናቶች በፊት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ መቀላቀሉ የሚወሳ ሲሆን አሁን ደግሞ የስምንት ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የአንድ ነባር ተጫዋች ውልም አራዝሟል።

ቡድኑን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ግብ ጠባቂ የሆኑት ስርጉት ተስፋዬ እና ባንቺአየው ደመላሽ ፣ ከወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ከተገኘ በኋላ በሊጉ ድንቅ ተሳትፎን እያደረገች ያሳለፈችው አጥቂዋ ንግስት በቀለን ፣ የአርባምንጭ ከተማዋ አጥቂ መሠረት ወርቅነህ ፣ የቀድሞዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዲስ አበባ እና አርባምንጭ አጥቂ ቤቴልሄም ሰማን ፣ በቦሌ ክፍለከተማ ድንቅ ጊዜ የነበራቸው አማካዮቹ ስንታየው ሂርኮ እና ትርሲት ወንድወሰን እንዲሁም የአርባምንጭ ከተማዋ ተከላካይ ቤቴልሄም ግዛቸው ይገኛሉ።

ክለቡ በአማካይ ስፍራ በክለቡ ቆይታ የነበራትን ገነት ኃይሉን ውል ሲያራዝም ቀድም ብላ ከክለቡ ጋር ተስማምታ ከነበረችው አጥቂዋ ዮርዳኖስ ምዑዝ ጋር ውል ማቋረጡን ክለቡ ለዝግጅት ክፍላትን የላከው መረጃ አመላክቷል።