ሁለት የጣና ሞገዶቹ ተጫዋቾች ስለነገው ጨዋታ ይናገራሉ….

👉”ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ውጤት አምጥተን ህዝባችንን ማስደሰት ነው የምናስበው” ቸርነት ጉግሳ

👉”ከፈጣሪ ጋር ጨዋታውን እናሸንፋለን ፤ ጥሩ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብዬ አስባለው” አለልኝ አዘነ

ቸርነት ጉግሳ

ዝግጅት እንዴት ነበር…

ዝግጅት ጥሩ ነው። ቡድኑን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተዘጋጀን ነው። ጥሩ ስብስብም ነው ያለን ፤ በአጠቃላይ አሪፍ ዝጅግት እያደረግን ነው።

ቡድኑ የተሟላ ዝግጅት አላደረገም ፤ አንተም ዘግይተህ ነው ስብስቡን የተቀላቀልከው። ይህ ምን ያህል ተፅዕኖ ይኖረዋል በጨዋታው?

አዎ! ተፅዕኖ ይኖረዋል ፤ ግን በቡድኑ ውስጥ ያለነው አብዛኞቹ ተጫዋቾች የምንተዋወቅ ስለሆነ አስፈላጊውን ልምምድ በተሟላ ሁኔታ ባንሰራም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ነገር እየሰራን ነው። የሰራነውንም ሜዳ ላይ የምንተገብር ከሆነ አሪፍ ነገር እናሳካለን ብዬ አስባለው።

የቡድኑ አዲስ ተጫዋች ነህ። ቡድኑን እንዴት አገኘከው?

አሪፍ ቡድን ነው። በስብስቡ ውስጥ በጣም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ጥሩ ስብስብ እንዲሁም ደስ የሚል መንፈስ ያለው ቡድን ነው። ጠንክረን ከሰራን ውጤት የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም።

ከአዛሙ ጨዋታ ምን እንጠብቅ?

ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ውጤት አምጥተን ህዝባችንን ማስደሰት ነው የምናስበው።

አለልኝ አዘነ

ለነገው ጨዋታ በምን አይነት መልኩ ተዘጋጃችሁ?

በጥሩ ሁኔታ ነበር ስንዘጋጅ የነበረው። በዋናነት እሁድ ነው ወደ ዝግጅት የገባነው። ባለችው አጭር ጊዜ በቀን ሁለት እንዲሁም አንድ ጊዜ ልምምዳችንን ስንሰራ ነበር። በአጠቃላይ ለነገው ጨዋታ ጥሩ እየተዘጋጀን ነው።

የዝግጅት ጊዜ ማጠር እንዳለ ይታወቃል። ይህ ምን ያክል ተፅዕኖ ያደርግባችኋል?

የዝግጅት ጊዜ ማጠሩ ትንሽ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ግን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካለቀ በኋላ ለእረፍት ብንወጣም ሁላችንም አልተኛንም። በግላችን ስንሰራ ነበር። ይሄ በትንሹም ቢሆን ተፅዕኖውን ይቀንሳል ብዬ አስባለው።

ባህር ዳር ከተማ በዚህ ውድድር በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚሳተፈው። ምናልባት ከልምድ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ? ስለ ተጋጣሚያችሁስ ምን ትላለህ?

ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በደንብ ነው ስንዘጋጅ የነበረው። ተጋጣሚያችን አዛም ትልቅ ቡድን ነው። ለጨዋታው በሚመጥን ሁኔታ በደንብ ተዘጋጅተን ነው ጨዋታውን እየተጠባበቅን የምንገኘው።

የባህር ዳር ከተማን መለያ ብትለብሱም ሀገርን ወክላችሁ ነው የምትጫወቱት። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ከጨዋታው ምን ይጠብቁ?

ከፈጣሪ ጋር ጨዋታውን እናሸንፋለን ፤ ጥሩ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብዬ አስባለው።