“የምንገጥመው ጠንካራውን አዛም ነው ፤ የእኛ ባህር ዳር ከተማም ጠንካራ ክለብ ነው” ደግአረገ ይግዛው

በነገው ዕለት ከታንዛኒው አዛም ጋር የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ያለው የባህር ዳር ከተማው ዋና አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ከጨዋታው በፊት ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።

ዝግጅት እንዴት ነበር?

ዝግጅታችን ቀደም ብለን በባህርዳር ለመጀመር ሞክረን ነበር። የተወሰኑ ቀናት ልምምድ ከሰራን በኋላ በተፈጠረው ነገር አስራ ሁለት ቀናት ከልምምድ ርቀን ነበር የቆየነው ፤ ሆኖም በተጀመረው ዐየር በረራ ወደ አዲስ አበባ መጥተን ያለፉትን አምስት ቀናት በአዲስ አበባ እየተዘጋጀን እንገኛለን። በእቅዳችን መሰረት ዝግጅታችን ባይሄድም በእነዚ አጭር ቀናት መስራት የሚገባንን ስራ ለመስራት ጥረት እያደረግን እንገኛለን። የተጫዋቾቻችን ዝግጁነት በጥሩ ሁኔታ ይገኛል። ነገ ላለብን ጨዋታ በተሻለ መንገድ ለመቅረብ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ዝግጅታችን ባቋረጥንበት ጊዜ ግን ብዙ እቅድ ነው ያበላሸብን። አንዱ ከዩጋንዳው ሞደርን ስፖርት ጋር እና ከአንድ የሱዳን ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ዝግጅት የጀመርንበት ጊዜ ነበር። ጨዋታዎቹ ትልቅ ጠቀሜታ ነበራቸው ፤ ተጫዋቾቻችን የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የሚያገኙበት ነበር። ለእዚ ጨዋታ ተገቢው ዝግጅት አድርገናል ብዬ ባላስብም ባለችው አጭር ቀን ተጫዋቾቻችን በአካል እና በስነ ልቦና ለማዘጋጀት ጥረት እያደረግን ነው። በነገው ጨዋታ የተሻለ ተፎካካሪ ሆነን እንቀርባለን ብዬ አስባለው።

ልምምዳችሁን በተሟላ ሁኔታ አለማከናወናችሁ ምን ያክል ተፅዕኖ አለው?

ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው። አንደኛ አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድናችን የተቀላቀሉበት ወቅት ነው። ሁለተኛ ደግሞ ውድድር ጨርሰን ከእረፍት የተመለስንበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቂ የዝግጅት ጊዜ አለማግኘታችን ተጫዋቾቹ ከማዋሀድ፣ አካል ብቃታቸው ከማሳደግ እና የምንፈልገው ነገር ለማስረፅ ትልቅ ተግዳሮት አለው። ግን ይህ ከእኛ አቅም በላይ በሆነ ነገር የተፈጠረ ችግር በመሆኑ በመፍትሔው ነው ያተኮርነው ፤ ስለዚህ ባገኘነው አጋጣሚ እዚህ አዲስ አበባ ለመሰባሰብ ነው የሞከርነው። እንደመጣን ደግሞ ወደ ስራ ለመግባት ጥረት አድርገን አዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ድጋፍ አድርጎልን አበበ ቢቂላ ስቴድየም ተጠቅመናል ፤ እንዲሁም ደግሞ የሜዳ ችግራችን ለመቅረፍ ባደረግነው ጥረት የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ሜዳን ሰጥተውናል። በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።

ታዲያ ባለችው አጭር ቀን ምን አይነት ዝግጅት አደረጋችሁ?

በእነዚህ አራት ቀናት ለመዘጋጀት በምናደርገው ጥረት ተጫዋቾቹን ከማዋሀድ ተያይዞ እና አካል ብቃታቸው ከማሳደግ ጥረት ስናደርግ ነው የቆየነው። ከሞላ ጎደል በምፈልገው ደረጃ ደርሰውልናል ብለን ባናስብም ባሉት ቀናት ግን የምንችለው ሁሉ ጥረት አድርገን ወደ ጨዋታ ለመግባት ነው የምናስበው።

ስለተጋጣሚያችሁ አዛም…

አዛም ትልቅ ክለብ ነው። አደረጃጀቱም ጠንካራ ነው። ጨዋታው ከማድረጉ በፊት ወደ አራት አምስት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርጓል። በበቂ ሁኔታ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ የነበረ ቡድን ነው። የተሟላ ቡድን ነው፤ ያንን እናውቃለን ተጫዋቾቻችንም ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርገናል። ትልቁ ነገር በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መወዳደር እና የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት መሆኑ ተጫዋቾቻችን ተገንዝበዋል። በተቻለኝ መጠን በስነ ልቦናው ለማዘጋጀት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው። የአህጉር አቀፍ ጨዋታዎች ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም አሉን፤ እነሱም ልምዳቸው እንዲያካፍሉ እያደረግን ነው። እርግጥ ነው የምንገጥመው ጠንካራውን አዛም ነው፤ የእኛ ባህር ዳር ከተማም ጠንካራ ክለብ ነው። በነገው ጨዋታ የተሻለ ነገር እናሳያለን ብዩ አስባለው።


አዲስ ተጫዋቾች ቡድኑን ከመቀላቀላቸው እና ከልምድ ጋር ተያይዞ ስላሉ ሁኔታዎች…

እኛ እንግዲህ ከውጪ ካመጣናቸው ተጫዋቾች ይልቅ ሀገር ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ላይ ትኩረት አድርገን በውድድሩ ላይ እንሳተፋለን ብዬ አስባለሁ። ልጆቹ አዳዲሶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አንድ ላይ በዚህ ክለብ አይጫወቱ እንጂ አንዳንዶቹ በተለያዩ ክለቦች አንድ ላይ የተጫወቱ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ አንድ ጥሩ አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል። እርስ በእርስም በቅርበት የሚተዋወቁ በመሆናቸው ለማላመድ ብዙ ችግር ይገጥመናል ብዬ አላስብም። ሆኖም ግን እግርኳስ በራሱ ቋንቋ ነው። ኳሱ ራሱ እንዲዋሀዱ አንድ ተጨማሪ ጉልበት ሆኖ ያገለግለናል። እንዳልከው አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ተቀላቅለዋል ፤ ጊዜ ይፈልጋሉ ከቡድኑ ጋር ሙሉ ለሙሉ ተዋህደው የምንፈልገውን ነገር ለማምጣት። ውድድሩም በቂ የዝግጅት ጊዜ ይፈልጋል ያንን የዝግጅት ጊዜ ማግኘት አልቻልንም ፤ እነዚህ እነዚህ ተግዳሮቶች ናቸው የሚሆኑት። ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነን ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት እንሞክራለን። የወከልነው ደግሞ ባህር ዳር ከተማን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ነው እና ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን በመቅረብ በምንችለው ሁሉ በሥነልቦናው ተዘጋጅተን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ ፤ ተጫዋቾች ጋር ያለውም ስሜት ይሄ ነው።