ሪፖርት | መድን ከወራጅ ቀጠናው ማምለጥ ተያይዞታል

የአቡበከር ሳኒ ሁለት የግንባር ግቦች ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን እንዲያሳካ ረድተዋል።

መድኖች ከባለፈው ሳምንት ቋሚ አሰላለፍ ተክለማርያም ሻንቆ፣ በርናንድ ኦቼንግ፣ ዮናስ ገረመው እና ብሩክ ሙልጌታን በአቡበከር ኑራ፣ ሰኢድ ሀሰን፣ አሚር ሙደሲር እና አብዲሳ ጀማል ተክተው ሲገቡ ሀምበሪቾዎች በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ ከተሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ አቤል ዘውዱ እና በኃይሉ ተሻገር በፍቃዱ አስረሳኸኝና ዘሩባቤል ፈለቀ ተክተው ገብተዋል።

የኢትዮጵያ መድን ሙሉ ብልጫ የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች ያስመለከተ ነበር። መድኖች በኳስ ቁጥጥርም ይሁን የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻሉ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ቢችሉም እንደነበራቸው ብልጫ በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም። ቡድኑ ምንም እንኳ ጥቂት ሙከራዎች ማድረግ ቢችልም የተፈጠሩት ዕድሎች ግን ጥራታቸው ላቅ ያሉ ነበሩ፤ በተለይም በአጋማሹ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ጄሮም ፊሊፕ አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና የመለሰው ኳስና አብዲሳ ጀማል በአቡበከርና ጄሮም ጥሩ ተግባቦት ወደ ግብ ክልል የደረሰችውን ኳስ መቶ ፓሉማ እንደምንም ያወጣት፤ እንዲሁም አብዲሳ ግብ ጠባቂው መልሷት በድጋሚ እግሩ ስር የገባችውን ኳስ መቶ ቶሎሳ ንጉሴ ከመስመሩ የመለሳት ኳስ መድኖችን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።

በቁጥር በዛ ባሉ ተጫዋቾች የተገነባ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው ሀምበሪቾዎች በውስን አጋጣሚዎች በረዣዥም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ከሞከሩባቸው ቅፅበቶች ውጭ በአመዛኙ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ አቀራረብ ነበራቸው። አብዛኛው የአጋማሹ ክፍለ ጊዜ ተነጥሎ የነበረው አንዱልከሪም ዱግዋ ከበረከት ወንድሙና አብዱልሰላም የሱፍ የተሻገሩለትን ኳስ ተጠቅሞ የፈጠራቸው ተስፋ ሰጪ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችም ይጠቀሳሉ።

ሁለተኛው አጋማሽ በኢትዮጵያ መድን ብልጫ ቢጀምርም ለግብ የቀረበ ሙከራ በማረግ ቀዳሚ የነበሩት ግን ሀምበሪቾዎች ነበሩ፤ አላዛር ከርቀት አክርሮ መቶት ግብ ጠባቂው እንደምንም ያወጣው ድንቅ ሙከራም ቡድኑን መሪ ለመድረግ ተቃርቦ ነበር። ከመጀመርያው አጋማሽ በአንፃራዊነት የተቀዛቀዘ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው መድኖች ከኳስ ቁጥጥር በዘለለ ግብ ሳያስቆጥሩ ቢዘልቁም በፊት መስመሩ ላይ ያደረጉት ስኬታማ ቅያሪ ጫና ከመፍጠር ባለፈ ግብ እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። በስልሳ ስምንተኛው ደቂቃም በአቡበከር ሳኒ አማካኘነት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል፤ አጥቂው ወገኔ ገዛኸኝ ከቆመ ኳስ ያሻማው ኳስ በግንባር በመግጨት ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኃላም ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው መድኖች የግብ ጠባቂው የውሳኔ ስህተት በአግባቡ ተጠቅመው ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ አቡበከር ሳኒ ተቀይሮ የገባው አለን ካይዋ በግንባር ያሻገረለትን ኳስ በግምባሩ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው ማስቀጠል ያልቻሉት ሀምበሪቾዎች በአጋማሹ በበፍቃዱ አማካኝነት ከርቀት ያደረጉት ሙከራ የተሻለ ለግብ የቀረበ ነበር። ጨዋታው መጠናቀቁ ተከትሎ መድን ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ማሳካት ችሏል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀምበሪቾ አሰልጣኝ ብሩክ ሲሳይ ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ እንደተንቀሳቀሰና የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ መግታት እንደቻለ ገልፆ የአየር ላይ ኳስ መከላከል ግን ጥሩ እንዳልነበሩ ገልጿል። አሰልጣኙ ቡድኑ በቻለው መጠን እስከ መጨረሻው እንደሚታገልም አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኋይሌ በበኩላቸው በመጀመርያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልነበሩ በመግለፅ ለዚህም የአጨራረስ ክፍተታቸው እንደምክንያት አቅርበዋል።በሁለተኛው አጋማሽ ያደረጓቸው ለውጦች ጥሩ ውጤት እንዳመጡ የገለፁት አሰልጣኙ ጨምረውም የፊት መስመር ተጫዋቾቹ እንቅስቃሴ ጥሩ እንደሆነ አንስተዋል።