ሪፖርት | በመጨረሻ ደቂቃ የተቆጠረች አከራካሪ ጎል ቡናማዎቹን ከንግድ ባንክ ነጥብ አጋርታለች

ኢትዮጵያ የሚለውን የሀገራችን ስም ያስቀደሙ ሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦች ያገናኘው ፍልሚያ አራት ጎሎች ተቆጥረውበት አቻ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎችም ሆነ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች አንድም ተጫዋች ሳይቀይሩ ተመሳሳይ ቀዳሚ አሰላለፍ ተጠቅመው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ ምንም እንኳን ዒላማውን የጠበቀ ባይሆንም የመጀመሪያው ሙከራ ተስተናግዷል። በዚህም የሊጉ መሪ የሆኑት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኪቲካ ጂማ አማካኝነት በጊዜ ቀዳሚ ለመሆን ጥረው ተመልሰዋል። ባንኮች በጊዜ መሪ ለመሆን የነበራቸው ውጥን በሀሳብ ብቻ አልቀረም። በዚህም በ5ኛው ደቂቃ ድንቅ አጀማመራቸውን በጎል አጅበዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ሱሌይማን ሀሚድ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት እና የግቡ አግዳሚ ተባብረው ሲመልሱት ሳጥን ውስጥ የነበረው ሳይመን ፒተር በአንድ ንክኪ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወዲያው ወደ እንቅስቃሴ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ9ኛው ደቂቃ አቻ ለመሆን እጅግ ተቃርበው ነበር። በዚህም አብዱልከሪም ወርቁ ፈቱዲንን በማለፍ ወደ ግብ የመታው ኳስ ቋሚውን ገጭቶ መክኗል። ይሁ ተጫዋች በ14ኛው ደቂቃ ሌላ ጥቃት ሰንዝሮ በተከላካዮች ተመልሶበታል። በኳስ ቁጥጥሩም ረገድ የተሻሉት ቡናማዎቹ የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው በማምጣት መንቀሳቀስ ይዘዋል። በ22 እና 23ኛው ደቂቃም ተከታታይ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች አድርገዋል። በቅድሚያ አንተነህ ተፈራ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ቀጥሎ ደግሞ አማኑኤል ዮሐንስ በተቃራኒ ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ በግንባራቸው ወደ ግብ ልከው ነበር።

ንግድ ባንኮች ጨዋታውን እየመሩ ቢገኙም ግብ ካስተናገዱ በኋላ ፍፁም በቡናማዎቹ ብልጫ ተወስዶባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያስተናገዱ ተስተውሏል። በተለይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አብዱልከሪም በግሉም ከቡድን አጋሮቹ ጋር እየተቀባበለ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ሲያደርግ የነበረው ነገር ፈተና ሆኖባቸዋል።

እንደብልጫቸው ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት በሰሩት የወረደ ስህተት የመዓዘን ምት ለተጋጣሚያቸው ሰጥተው ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በ44ኛው ደቂቃ ፉዐድ ፈረጃ ያሻማውን ኳስ ሳይመን ፒተር ራሱን ለጉዳት ዳርጎ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። አጋማሹም በባንክ 2ለ0 መሪነት ተፈፅሟል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ቡናማዎቹ ከጎል ጋር የሚያስታርቃቸውን ባንኮች ደግሞ ጨዋታውን የሚቆጣጠርላቸውን አማራጭ ለመጠቀም ሞክረዋል። ይህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደ መጀመሪያው ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎች ያልተደረገበት ነበር። ቡናዎችም ደቂቃ በደቂቃ ግብ አለማስቆጠራቸው እያቀዘቀዛቸው መጥቶ የባንክን የግብ ክልል መጎብኘት ላይ ተዳክመዋል። ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ጨዋታው የሚፈልገውን አጨዋወት እየተከተሉ በጨዋታው ቆይተዋል።

በአንፃራዊነት ቡናዎች በላይኛው ሜዳ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ በማሳደግ በቀረው ደቂቃ ቢያንስ አቻ ለመሆን ቢጥሩም ባንኮች መቀመስ አልቻሉም። ይባስ በ76ኛው ደቂቃ የአሠልጣኞች ነፃነት ተጫዋቾች ለማጥቃት በወጡበት ቅፅበት በተፈጠረ የቅብብል ስህተት ባንክ ብልጫውን ወደ ሦስት ሊያሳድግ ነበር።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ድንቅ ግብ ታይቷል። በዚህም ቡናማዎቹ የረፈደ ቢመስልም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው አማኑኤል ዮሐንስ ድንቅ ግብ ባንክ ጫና ውስጥ ከተዋል። በቀሪ ደቂቃዎች ቡናማዎቹ በከፍተኛ መነቃቃት ከየአቅጣጫው ጥቅት በመሰንዘር አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረት አድርገዋል። ቡናማዎቹ ውጥናቸው ሰምሮም ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመረው 4 ደቂቃ አጋማሽ ግብ አግኝተዋል። በድራማዊ ትዕይንት የቀጠለው ፍልሚያው በተጠቀሰው ደቂቃ በረጅሙ የተሻማን ኳስ ብሩክ እና መስፍን በግንባራቸው ሲገጩት የባንኩ ተከላካይ ፈቱዲን ነክቷት ወደ ጎል አምርታ የመስመር ዳኛው ጎሉን አፅድቀው ቡናማዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል። ጨዋታውም 2ለ2 ተደምድሟል።

ከጨዋታው በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው አሠልጣኝ ነፃነት ክብሬ በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ የግብ እድሎችን ቢያገኙም መጠቀም እንዳልቻሉ ገልፀው ተጫዋቾቻቸው በከፈሉት መስዋትነት አንድ ነጥብ በማግኘታቸው ደስታ እንደተሰማቸው አውስተው ተጫዋቾቻቸውን አመስግነዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንሉ አሠልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ በበኩላቸው በጨዋታው ጥሩ የነበሩ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከልክ ካለፈ ፍላጎት ከእቅዳቸው እንደወጡ ተናግረው በዚህ ምክንያት ጨዋታው ከእጃቸው እንደወጣ ተናግረዋል። በመጨረሻው ደቂቃ ስለተቆጠረባቸው አከራካሪ ጎልም አሠልጣኙ ምስሉን እያዩ “ይሄንን ጎል ማለት ይከብዳል” ብለዋል።