መረጃዎች | 92ኛ የጨዋታ ቀን

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

እንደ አዳማ ቆይታቸው ሁሉ የድሬዳዋ ቆይታቸውን በሽንፈት ያጠናቀቁት ሲዳማ ቡናዎች በነገው ዕለት በመቀመጫ ከተማቸው ሀዋሳ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በተለይም በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታቸው ብርቱ ፉክክር አድርገው በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረባቸው ጎል በንግድ ባንክ ቢሸነፉም ያሳዩት ጠንካራ እንቅስቃሴ ለቡድኑ ደጋፊዎች ተስፋ የሚሰጥ ነበር።

ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች በአምስቱ ጎል ማስቆጠር ያልቻሉት ሲዳማ ቡናዎች የነገውን ተጋጣሚያቸውን ወላይታ ድቻን በመጀመሪያው ዙር አራት የተለያዩ ተጫዋቾች ባስቆጠሯቸው አራት ጎሎች 4-1 ማሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን በዛ ጨዋታ ላይ የነበራቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ መልሶ ማግኘት የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ዋና የቤት ሥራ ነው።

ከተከታታይ ስምንት ድል አልባ ሳምንታት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች በግሩም ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኛሉ። በተለይም ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ቢኒያም ፍቅሩ የፊት መስመሩ ላይ የሚያደርገው ዕረፍት የለሽ ማራኪ እንቅስቃሴ ለቡድኑ ቁልፍ እየሆነ መጥቷል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 አሸንፈው ወደ ዋንጫው ማለፋቸውን ያረጋገጡት የጦና ንቦቹ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ሊያሳስባቸው የሚችለው ብቸኛው ነገር በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ ድል ሲቀዳጁ በኳስ ቁጥጥሩ የተወሰደባቸው ከፍተኛ ብልጫ ነው። ሆኖም በነገው ዕለት ሲዳማ ቡናን ረትተው በ9ኛው እና በ10ኛው ሳምንት ያሳኩትን ተከታታይ ድል ከ13 ሳምንታት በኋላ ለመድገም ጠንካራ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በሲዳማ ቡና በኩል ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን እና ጊት ጋትኮች በቅጣት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበቱት መልካሙ ቦጋለ እና ፀጋዬ ብርሃኑ ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 19 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና አስር ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 32 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 10 ፣ ሲዳማ ቡና 22 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ፋሲል ከነማ

በምሽቱ መርሐግብር የሚደረገው የነብሮቹ እና የዐፄዎቹ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀምበርቾን እና አዳማ ከተማን በተከታታይ አሸንፈው ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉት ሀዲያዎች ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግን በሲዳማ ቡና ሲሸነፉ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ግብ ተለያይተዋል። በተለይም ከጣና ሞገዶቹ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ፈታኝ ሆኖ አለመቅረቡ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስቆጥሩ እንዲወጡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።

በሊጉ ዝቅተኛውን ሽንፈት(3) እና ዝቅተኛውን ጎል(14) ያስተናገዱት ነብሮቹ ስድስት ጨዋቻዎችን አሸንፈው ከፍተኛውን የአቻ ውጤት(13) ያስመዘገቡ ሲሆን ተደጋጋሚውን የአቻ ውጤት ወደ ድል መቀየር ይጠበቅባቸዋል። በነገው ዕለትም በመጀመሪያው ዙር 2ለ1 ካሸነፉት ፋሲል ከነማ ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።

በድሬዳዋ ከተማ ቆይታቸው በ16ኛው ሳምንት ሀዋሳን 2ለ1 በ17ኛው ሳምንት ደግሞ ኢትዮጵያ መድንን 2ለ0 ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ አቻ ተለያይተው በድሬዳዋ ከተማ የተሸነፉት ፋሲል ከነማዎች ከጨዋታ ጨዋታ በውጤት ረገድ እየተቀዛቀዙ ይገኛሉ።

በየሳምንቱ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ምክንያት በማጣት የተሟላ ቡድን ይዘው ለመቅረብ የተቸገሩት ዐፄዎቹ ከመሪው ንግድ ባንክ 14 ነጥቦች ርቀት ላይ የሚገኙ ሲሆን በተለይም ባለፈው ሳምንት ከ 9 ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተው ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ በተለያዩበት ጨዋታ ጎልቶ እንደወጣው ጃቢር ሙሉ ዓይነት ታዳጊዎችን ዕድል በመስጠት ለቀጣይ ዓመት የሚጠበቅ ቡድን ማዘጋጀት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቤት ሥራ ነው።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል መለሰ ሚሻሞ እና ግርማ በቀለ በጉዳት ምክንያት የማይኖሩ ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት አማኑኤል ገብረሚካኤል እና አፍቅሮተ ሰለሞን በተጨማሪ ይሁን እንዳሻው በጉልበት ጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ላይ አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለሰባት ጊዜያት ተገናኝተው ሦስቱ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀው ፋሲል ከነማ 3 ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ በመጀመሪያው ዙር 1 ጊዜ አሸንፈዋል። በጨዋታዎቹም ዐፄዎቹ 9 ነብሮቹ ደግሞ 6 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።