የከፍተኛ ሊግ ውሎ

በርካታ የአቻ ውጤቶች ተመዝግበው በዋሉበት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዛሬ ጨዋታዎች ከምድብ ሀ ኮልፌ ቀራኒዮ ከምድብ ለ ደብረብርሀን ከተማ አሸናፊ ሆነዋል።

ምድብ ለ

ደብረብርሀን ከተማ ከቢሾፍቱ ከተማ ያደረጉት የእለቱ የመጀመርያ ጨዋታን ደብረብርሀኖች በመጀመርያ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3-2 አሸንፈዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ የበላይነት ማሳየት የቻሉት ደብረብርሀኖች በ21ኛው ደቂቃ ጎል አስቆጥረዋል። አብርሀም ምህረት ከርቀት የመታት ኳስ የግብ ጠባቂው ዝንጉነት ታክሎ ወደ ጎልነት ተቀይራ መሪ የሆኑ ሲሆን 29ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ማሞ አየለ የመታውን ኳስ ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ በግንባር ገጭቶ ለማውጣት ሲጥር በራሱ ላይ ተቆጥሮ መሪነታቸውን አስፍተዋል። የመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ደግሞ ማሞ አየለ ከመስመር ይዞ በመግባት መትቶ በማስቆጠር በ3-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት በፊት ተዳክመው የታዩት ቢሾፍቱዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው መቅረብ የቻሉ ሲሆን 57ኛው ደቂቃ ላይ አብዱላዚዝ ኡመር ከዳዊት ሺፈራው የተሻገረለትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮ ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። ጎሉ ያነቃቸው ቢሾፍቱዎች ጥቃታቸውን በመጨመር 72ኛው ደቂቃ ላይ ነጋሽ ታደለ ባስቆጠረው ጎል ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ሆኖም ጫና ፈጥረው በመጫወት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው በደብረብርሀን 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በእለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ከአዲስ ከተማ አቻ ተለያይተዋል። ወሳኝ መርሐ ግብር እንደመሆኑ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻዎች አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች መሪ መሆን ችለው ነበር። ቢላል ገመዳ 16ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ አስቆጥሮ መሪ ሲያደርግ 26ኛው ደቂቃ ላይም አንድ ሁለት ተቀባብሎ በመግባት ራሱ ቢላል ገመዳ አስቆጥሮ 2-0 መምራት ችለዋል።

ከጎሎቹ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የተንቀሳቀሱት አዲስ ከተማዎች 31ኛው ደቂቃ ላይ ልዩነቱን አጥብዋል። አህመድ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቅዱስ ተስፋዬ አስቆጥሯል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተጨራርፋ ስትመለስ ከሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ ያገኛት ቦጃ ኤደቻ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ አዲስ ከተማን አቻ በማድረግ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ አዲስ ከተማዎች ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ወሎ ኮምቦልቻዎች ኃይል የቀላቀለ አጨዋወት ተስተውሎባቸዋል። ሆኖም ከእንቅስቃሴ በዘለለ በሁለቱም በኩል ጥቂት የጎል እድሎች የተገኙ ቢሆንኝ መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ምድብ ሀ

የምድብ ሀ 23ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ሲገባደድ ሶስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀው ኮልፌ ቀራኒዮ ተጋጣሚውን በማሸነፍ የእለቱ ብቸኛ ባለድል ሆኗል።

ረፋድ ሶስት ሰዓት ላይ በተካሄደው ጨዋታ ስልጤ ወራቤ ከወልዲያ ተገናኝተው ያለ ግብ ተለያይተዋል። በረፋዱ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ባላቸው ጉጉት በፈጣኝ መልሶ ማጥቃት ቶሎ ቶሎ ወደተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ሲደርሱ ለመመለከት ተችሏል። የግብ ማግባት እድል በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ስልጤ ወራቤዎች በሚያደርጉት ረጃጅም ኳሶች ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎት መፍጠር ቢችሉ በደካማ አጨራረስ ሲያመክኑ ተስተውለዋል። ወልዲያዎችም በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማግባት ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካለቸው አልቻለም በዚህም የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለግብ ተለያይተው ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ግብ ለማስቆጠር ኳስ ይዘው በግቡም በሁለቱም ቡድን በኩል ጥሩ ሆኖ የዋሉት ተከላካዮቻተው ኳሶች ቶሎ ቶሎ ከግብ አከባቢ ሲያርቁ ተስተውሏል። አንዳንድ ወደግብ ሚደርሱ ኳሶችንም ሳይጠቀሙ ቀርተው ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ግድ ሆኗል።

ሁለተኛው ጨዋታ አምስት ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከጅማ አባጅፋር አገናኝቶ 1-1 ተጠናቋል። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የጨዋታ ብልጫ የወሰደው ጅማ አባ ጅፋር ግብ ለማስቆጠር የተሻለ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝተዋል። በ18ኛው ደቂቃ የአዲስአበባ ከተማ ተከላካዮች ባደረጉት እጅ ንኪኪ ፍፁም ቅጣት ምት ለጅማ አባ ጅፋር ተስጥቷቸው ፊልሞን ገ/ፃዲቅ ወደግብነት ቀይሮ ጅማ አባጅፋርን መሪ አድርጓል። የአቻነት ግብ ፍለጋ አዲስአበባ ከተማዎች ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ በ21ኛው ደቂቃ ናትናኤል አበበ በቅብብል ከርቀት የመታት ኳስ የግብ ቋም ብረት የመለሰበት አደገኛ ሙከራ ሲታወስ በርከት ያለ ሙከራ አድርገው የጥረታተው ውጤት የሆነችዋን ግብ መረብ ላይ አክለዋል። በ38ኛው ደቂቃ የአቻነቷን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። ኤርሚያስ ሀይሉ እየገፋ ሄዶ ያለቀ ኳስ አቃብሎለት ቢኒያም ታከለ ከመረብ ጋር አገናኝቷት አቻ ሆነው ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲመለስ ጨዋታውን ለመቀየር የተጫዋች ቅያሪ ቢያደርጉም እምብዛም የግብ ማጅባት ሙከራም ሆነ ሳቢ አጨዋወት መመለከት አልተቻለም። በዚህህ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።

ሌላኛው የ8:00 ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማን ከሞጆ ከተማ አገናኝቶ 1-0 በሆነ ውጤት በኮልፌ ቀራኒዮ አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋሜሽ ሁለቱም ግብ ሳያስቆጥሩ ሲለያዩ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ኮልፌ ቀራኒዮ በፍርድአወቅ ሲሳይ አማካኝነት በ53ኛው ደቂቃ ባስቆጠሩት ግብ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

ሌላኛው የሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ አስቀድሞ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከቤንች ማጂ ቡና አገናኝቶ ያለግብ ተጠናቋል።