መረጃዎች| 91ኛ የጨዋታ ቀን

በ23 ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚከናወኑ ሁለት መርሀ-ግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች

ኢትዮጵያ መድን ከ ሀምበሪቾ

ላለፉት አምስት ጨዋታዎች ከሽንፈት መራቃቸውን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው በስድስት ነጥቦች የራቁት መድኖች የአሸናፊነት መንገዳቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት መቻልና የቅርብ ተቀናቃኛቸው ወልቂጤ ከተማን በተከታታይ ያሸነፈው ቡድኑ ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ትልቅ መሻሻል አሳይቷል። መድኖች በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተከታታይ ድሎች ከማስመዝገባቸው በተጨማሪ ባለፉት አምስት መርሀ-ግብሮች ሽንፈት አላስተናገዱም። በነገው ዕለት ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣትም ከአደጋው ቀጠና ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ አስፈላጊነቱ ትልቅ ነው። ይህንን ተከትሎ ባለፉት መርሐ – ግብሮች በአመዛኙ ፈጣን ሽግግሮችና ቀጥተኛ አጨዋወቶችን በመተግበር የተሳካ የማጥቃት አጨዋወታቸው ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል ጎሎችን ለማግኘት እንደሚጥሩ ይታሰባል። ቡድኑ ድል ባደረገባቸው ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመርም ፍሬአማ ጉዞው ማስቀጠል ይኖርበታል።

በ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው የነገው ተጋጣሚያቸው መድን በአስራ አራት ነጥቦች ርቀው በሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጡት ሀምበሪቾዎች በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው እየተሟጠጠ ይገኛል። ካለፉት አስር መርሀ-ግብሮች ሁለት ነጥቦች ብቻ ማሳካት የቻለው ቡድኑ በቀሪ ጨዋታዎች ከድል በታች ያሉ ውጤቶች ማስመዝገብ በሊጉ አያተርፉትም። በተለይም በእንደ ነገ አይነት ከቅርብ ተፎካካሪዎች ጋር በሚደረግ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ መሰብሰብ የመትረፍ ዕድሉ በውስን መልኩ ስለሚያሰፋለት ጨዋታውን የማሸነፍ ግዴታ አለበት።

አስር ግቦች ብቻ ያስቆጠሩት ሀምበሪቾዎች ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረ ጨዋታ በውድድር ዓመቱ ለሦስተኛ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ቢችሉም በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ባስተናገዱበት የመጨረሻ ጨዋታ ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በቀጣይ ጨዋታዎችም የግብ ማስቆጠር ክፍተታቸው መቅረፍ ካልቻሉ ነጥብ ለማግኘት መቸገራቸው አይቀሪ ነው። በነገው ዕለት ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ የተከላካይ ክፍል ስለሚገጥሙ የማጥቃት አጨዋወታቸው ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ዳዊት እና ንጋቱ ገ/ሥላሴ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ ሲያልፋቸው ባለፉት ሳምንታት ቅጣት ላይ የሰነበተው አብዲሳ ጀማል ግን ነገ የሚመለስ ይሆናል። ሀምበሪቾዎች በበኩላቸው ጉዳት ላይ ያለውን ዳግም በቀለ አያሰልፉም።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመርያው ዙር ለመጀመርያ ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ መድን 2-0 አሸንፏል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሀ-ግብር የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ወደ ፍፃሜው የሚያሻግራቸው ድል ያፈሱት ቡናማዎቹ ከወሳኙ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ያገኙት የአሸናፊነት ስነ-ልቦና በጨዋታው እንዲጠበቁ ያደርጋቸዋል። ባለፉት መርሀ ግብሮች ነጥቦች መጣላቸውን ተከትሎ ከመሪው በአስራ ሁለት ነጥቦች ለመራቅ የተገደዱት ቡናማዎች ከተከታታይ ድሎች በኋላ ውስን መቀዛቀዞች አሳይተዋል። ቡድኑ ከመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለውም በአንዱ ብቻ ነው። ለቡድኑ መቀዛቀዝ እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥም የፊት መስመሩ ውጤታማነት መቀነስ አንዱ ነው። ከዚ ቀደም ከቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎኖች አንዱ የነበረው ጥምረቱ አሁንም በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ቢገኝም የአፈፃፀም ደረጃው መውረድ ቡድኑ ውጤት ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል። የፊት መስመሩ አሁንም በጥሩ ብቃት ላይ እንዳለ መቻልን በገጠመበት የሊጉ የመጨረሻ ብያስመሰክርም ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ክፍተቱን መቅረፍ ግድ ይለዋል።

በአምስት ነጥቦች ልዩነት ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ንግድ ባንኮች ነገ የዋንጫ ጉዟቸው ሊወስኑ ከሚችሉ ወሳኝ መርሀ-ግብሮች አንዱ የሆነውን ጨዋታ ያከናውናሉ። ንግድ ባንኮች ከሳምንታት በፊት በሦስት ተከታታይ መርሀ-ግብሮች ውድ ነጥቦች ቢጥሉም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አሸንፈው የተቀናቃኞቻቸው ነጥብ መጣል በአግባቡ ተጠቅመውበታል። ቡድኑ አብዝቶ የሚጠቀምበት መስመሮች ላይ የተመሰረተ የማጥቃት አቀራረብ እንደሚኖረው ቢጠበቅም የተጋጣሚው ፈጣን ሽግግር አጨዋወቱን ከፍ ባለ ነፃነት እንዳይተገብረው ሊያግደውም ይችላል። ባለፉት ጨዋታዎች ከባድ ፈተናዎች የገጠሙት የንግድ ባንክ የመከላከል አደረጃጀት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ በመጨረሻው መርሀ-ግብር መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። በመጨረሻ ጥሩ የሆነለትን የመከላከል ሪከርዱን አስጠብቆ ለመጨረስ ግን የቡናማዎቹ ፈጣን ጥቃቶች የማቋረጥ አቅሙን ከፍ አድርጎ መገኘት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 34 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 18 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። ባንክ 9 ሲያሸንፍ በቀሪው 8 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 54 ጎሎች ፣ ባንክ 37 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።