ከፍተኛ ሊግ | አርባምንጭ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አጋግጧል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 23 ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች በምድብ ለ አርባምንጭ ከተማ ወደ 2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠበትን ድል ሲያስመዘግብ ነገሌ አርሲ እና ደሴ ከተማ አሸንፈዋል። የምድብ ለ ደግሞ ንብ እና ነቀምቴ ድል ቀንቷቸዋል።

በምድብ ለ የእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ቦዲቲ ከተማን በማሸነፍ የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎውን አረጋግጧል። ጥሪ እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጎል ያልተቆጠረበት ሲሆን በቦዲቲ በኩል ዮርዳኖስ ኢያሱ ከርቀት የሞከራት እና በአርባምንጭ በኩል ከእንዳልካቸው መስፍን የተሻገረውን አስራት መገርራ በግንባሩ ገጭቶ ሞክሮ የወጣበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ የማጥቃት ኃይላቸውን አጠናክረው የገቡት አርባምንጮች ድል ያስመዘገቡባቸውን ጎሎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አስቆጥረዋል። ተቀይሮ የገባው ቡታቃ ሻመና 87ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቀዳሚ ሲያደርግ ሌላው ተቀይሮ የገባው ዘካርያስ ፍቅሬ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ከእንዳልካቸው ተመትቶ የተመለሰውን ኳስ አግኝቶ በማስቆጠር ጨዋታው በአርባምንጭ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አዞዎቹም አምና በሀዘን የተሰናበቱትን ፕሪምየር ሊግ ለከርሞ መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።

በሁለተኛው የእለቱ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻን የገጠመው ነገሌ አርሲ 2-1 አሸንፏል። እንደመጀመርያው ጨዋታ ሁሉ አንደኛው አጋማሽ ላይ ጎል ያልተቆጠረበት ጨዋታው በጋሞ ጨንቻዎች በኩል በ25ኛው ደቂቃ ላይ ወደፊት ይዘው ገብተው ሞክረው ተከላካዩ ቦና ያወጣባቸው ሙከራ ሲጠቀስ በነገሌ አርሲ በኩል ጀቤሳ ሚኤሳ በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች እድሎች አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀምባቸው የቀራቸው ይጠቀሳሉ።

ከእረፍት መልስ ተነቃቅተው የገቡት ነገሌ አርሲዎች በተከታታይ ጎል አግኝተዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ተስፋዬ ከመስመር ያገኘውን ኳስ አስቆጥሮ መሪ ሲያደርግ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ጋሞዎች ለማጥቃት በሄዱበት ወቅት የተቋረጠውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ሰለሞን ገመቹ አቀብሎት ጀቤሳ ሚኤሳ የበረኛውን መውጣት ተመልክቶ አስቆጥሮ መሪነቱን አስፍቷል።

ከጎሎቹ በኋላ ጎል ለማስቆጠር የተሻለ ጥረት ያደረጉት ጨንቻዎች በ77ኛው ደቂቃ ያሬድ መኮንን በራሱ ጥረት ይዞ በመግባት አክሮ መትቶ ባስቆጠረው ጎል ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በነገሌ አርሲ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ደሴ ከተማ እና አቡሽ ደርቤ ደምቀው በዋሉበት የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ደሴ ባቱን 4-1 አሸንፏል። 13ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግርማ ከሳጥን ውጪ በመምታት ባስቆጠረው ጎል ደሴዎች ቀዳሚ የሆኑ ሲሆን 19ኛው ደቂቃ ጆቴ ገመቹ ያመቻቸለትን ዝነኛው ጋዲሳ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣችበት ባቱዎች ያገኙት መልካም አጋጣሚ ነበር። በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳዩት ደሴዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ከፀጋ ደርቤ የተሻገረለትን አቡሽ ደርቤ አስቆጥሮ መሪነታቸውን አስፍተው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ እንደመጀመርያው ሁሉ የበላይነት የነበራቸው ደሴዎች በ53ኛው ደቂቃ አቡሽ ደርቤ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደ ጎችነት በቀየረው ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሦስት ሲያሰፉ 66ኛው ደቂቃ ላይ አቡሽ ደርቤ ከታናሽ ወንድሙ ፀጋ ደርቤ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ይዞ በመግባት ሐት ትሪክ የሰራበትን ጎል አስቆጥሯል። ባቱዎች ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ዳዊት አሸናፊ አስቆጥሮ ጨዋታው በደሴ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ላይ በምድብ ለ የ23ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የረፋድ ጨዋታ ንብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኦሮሚያ ፖሊስን 4-0 አሸንፏል። ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ባስመለከተው የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ብልጫ ለመውሰድ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። በ44ኛው ደቂቃ ላይ የኦሮሚያ ፖሊሱ 6 ቁጥር ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ የመታትን ኳስ የንቡ ግብ ጠባቂ እንዴትም ሆኖ ያዳነው ሙከራ ይታወሳል። ሆኖም ግን የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ሳያስመለክት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ብሎ የገቡት ንቦች ግቦችን ማምረት ችለዋል። በ60ኛው ደቂቃ ደቂቃ ከመሀል አከባቢ የተሻማውን ኳስ የኦሮሚያ ፖሊሱ ግብ ጠባቂ መቆጣጠር ተስኖት ኳሷ ሲታመልጠው የንብ ተከላካይ ኪም ላም አግኝቶ ከመረብ ጋር አገናኝቷታል። በ70ኛው ደቂቃ የሚያምር ቅብብል በማድረግ ንቦች ወደፊት ሲሄዱ ምስክር መለስ በግሩም ሁኔታ ከፍ አድርጎ የለጋውን ኳስ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ የገባው ባሕሩ ፈጠነ በጥሩ አጨራረስ ኳስና መረብ አገናኝቶ መሪነታቸውን ወደሁለት ከፍ አድርጓል። በ80ኛው ደቂቃ ናትናኤል ሰለሞን ከመሃል ሜዳ አከባቢ ኳስ እየገፋ ይዞ ገብተው ጨርሶ ያቀበለውን ኳስ እዮብ ደረሰ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸውን አስፍቷል። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል ተጨማሪ በታየው ላይ ናትናኤል ሰለሞን በራሱ ጥረት የኦሮሚያ ፖሊስ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ አራተኛ ግብ መረብ ላይ አክሎ ጨዋታው በንብ 4-0 ተጠናቋል።

10:00 ላይ በተደረገ ጨዋታ ነቀምቴ ከተማ ሀላባ ከተማን 2-0 ማሸነፍ ችሏል። በአንደኛው አጋማሽ ያለግብ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በጥንቃቂ ተጫውተው የመጀመሪያውን አጋማሽ ያሳለፉ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነቀምቴ ከተማ አሸናፊ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የነበሩት ነቀምቴ ከተማዎች ከእረፍት መልስ ግብ አክለዋል። በ52ኛው ደቂቃ ተመስገን ዱባ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ነቀምቴ ከተማን መሪ ማድሪግ ችሏል። በዚህ ብቻ ያላበቁት ነቀምቴዎች ተጨመሪ ግብ በ67ኛው ደቂቃ ከመረብ ጋር አገናኝተዋል። በጨዋታው ጥሩ በመንቀሳቀስ ኮከብ ተጫዋች የተባለው ግሩም ግዛው በ67ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቶ ነቀምቴ ከተማ 2-0 እንዲያሸንፍ ሆኗል።