ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ተከታታይ ድል አሳክተዋል

ባህር ዳር ከተማ በሀብታሙ ታደሰ ብቸኛ ግብ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 በመርታት ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።

የጣና ሞገዶቹ በ19ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን 2ለ1 ሲያሸንፉ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ብርቱካናማዎቹ በአንጻሩ በ22ኛው ሳምንት ሻሸመኔን 1ለዐ ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ አቤል አሰበ እና አሜ መሐመድ አስወጥተው ዳግማዊ ዓባይ ፣ ሱራፌል ጌታቸው እና ያሬድ ታደሰ ተክተው ገብተዋል።

12 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ መሪነት የጀመረው ጨዋታው ዝግ ያለ አጀማመር ያስመለከተን ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ በአጋማሹ የመጀመሪያ ሩብ ደቂቃዎች የግብ ዕድሎችን አላስመለከተንም ነበር።

ጨዋታው 17ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጣና ሞገዶቹ በግሩም የቡድን ሥራ ግብ አስቆጥረዋል። በቀኝ መስመር ከፈጣን የእጅ ውርወራ የተነሳውን ኳስ ፍጹም ጥላሁን እና ፍሬው ሰለሞን ከተቀባበሉ በኋላ ኳሱን ያገኘው ቸርነት ጉግሳ በውጪ እግሩ ያቀበለውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በተረጋጋ አጨራረስ መሬት ለመሬት በመምታት ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፉታል።

በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች 23ኛው ደቂቃ ላይ በፍሬው ሰለሞን 26ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሀብታሙ ታደሰ ተጨማሪ ጥሩ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለው ነበር።

34ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አንጃውን አስወጥተው አቤል አሰበን ያስገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጠኑ እየተነቃቁ በመሄድ 40ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ያሬድ ታደሰ ከካርሎስ ዳምጠው ጋር ተቀባብሎ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ሱራፌል ጌታቸው በግሩም ክህሎት ግብ ጠባቂውን ፔፔ ሰይዶን በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ፍጹም ፍትሕዓለው በድንቅ ቦታ አያያዝ በግንባሩ በመግጨት አስወጥቶበታል።

የጣና ሞገዶቹ መሪነታቸውን አጠናክረው ወደ ዕረፍት ሊያመሩ የሚችሉበትን አጋጣሚ 44ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረው ቸርነት ጉግሳ ከሀብታሙ ታደሰ በተቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ የጣና ሞገዶቹ ቸርነት ጉግሳን በመጠነኛ ጉዳት ምክንያት በማሳረፍ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ያስፈረሙትን ጸጋዬ አበራን ሲያስገቡ ከጋማሹ ክፍት የነበረ ቢመስልም ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ኳሶች የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩበትም ነበር።

ቀዝቃዛ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች 59ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የነበረ ሲሆን ፍሬው ሰለሞን ያሻገረለትን ኳስ በደረቱ ያበረደው ጸጋዬ አበራ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዓብዩ ካሣዬ አውጥቶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ራሱ ጸጋዬ ከሳጥን ውጪ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር።

በተመሳሳይ ሂደት በቀጠሉት የመጨረሻ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች 84ኛው ደቂቃ ላይ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረው ያሬድ ታደሰ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አቤል አሰበ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ሲያድንበት በ90ኛው ደቂቃ ላይ የባህር ዳሩ ፍጹም ጥላሁን 90+3ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የድሬዳዋው አቤል አሰበ ካደረጓቸው ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ ተጨማሪ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳያስመለክተን ጨዋታው በባሕር ዳር ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ አጀማመራቸው ጥሩ እንዳልነበር ጠቁመው የግብ ዕድሎችን አለመጠቀማቸው ለሽንፈት እንደዳረጋቸው በመግለፅ ቻርለስ ሙሴጌን በቋሚ አሰላለፍ ያላካተቱት ከጉዳት በመመለሱ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል። የባህር ዳር ከተማው ምክትል አሰልጣኝ መብራቱ ሀብቱ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ እንደፈለጉት መቅረባቸውን በመናገር በሁለተኛው አጋማሽ ግን ውጤቱን ለማስጠበቅ ከመፈለጋቸው አንፃር እንቅስቃሴያቸውን እንዳላስቀጠሉ ጠቁመው በጉዳት ምክንያት ቡድናቸው እየታመሰ እንደሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።