የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ከነገው ጨዋታ በፊት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል…

“…በእርግጥ አሸንፈን መምጣታችን በተወሰነ መልኩ ጨዋታው ያለቀ አይነት ስሜት ሊፈጥር ይችላል ፤ ነገርግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ይህ እሳቤ አይሰራም” ቢኒያም በላይ

“ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁላችንም ከልጅነታችን ጀምሮ የምንመኘው ትልቅ ክለብ ነው” ፋሲል ገብረሚካኤል

ቢኒያም በላይ

ለመልሱ ጨዋታ ስላደረጉት ዝግጅት…

“ዝግጅት አሪፍ ነው ፤ ከታንዛንያ መልስ በነበሩት ቀናት ቢሾፍቱ ላይ እና እዚህ አዲስ አበባ ላይ በሚገባ ለጨዋታው ትኩረት ሰጥተን ዝግጅት አድርገናል።”

ከሜዳ ውጭ ያስመዘገቡት ድል በነገው ጨዋታ ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ…

“በእርግጥ አሸንፈን መምጣታችን በተወሰነ መልኩ ጨዋታው ያለቀ አይነት ስሜት ሊፈጥር ይችላል ፤ ነገርግን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ይህ እሳቤ አይሰራም። ቡድናችን ሁሌም አሸናፊ ለመሆን ነው የሚጥረው ፤ በተጨማሪም በአፍሪካ መድረክ ላይ ደግሞ የተሻለ ርቀት መጓዝ ውጥናችን ነው። ስለዚህ የትኛውንም ጨዋታ ቀለል አድርገን አንመለከትም።”

በመልሶ ጨዋታ ደጋፊዎች ከእሱ ምን እንደሚጠብቁ…

“ፈጣሪ ይመስገን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ጥሩ ነገሮችን አሳክቻለሁ ፤ ወደዚህ የመጣሁት ቡድኑን ለማገዝ ነው በግሌም እንደተጫዋች ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ መሸጋገር እፈልጋለሁ። ለዚህም በየጨዋታው ተፅዕኖ ማሳደር አለብኝ። በመሆኑም በነገው ጨዋታ እንደ ቡድን ሆነ በግሌ የቻልነውን እንሰጣለን።”

ፋሲል ገ/ሚካኤል

ስለነገው ጨዋታ ዝግጅታቸው…

“በቂ ጊዜ ስለነበርን የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ ጥረናል ፤ ሁሉም የቡድናችን አባል ከፍ ባለ ተነሳሽነት እየተዘጋጀን እንገኛለን። ለነገውም ጨዋታ ሁላችንም ዝግጁ ነን።”

አዲሱ ቡድኑ ውስጥ ስላለው ስሜት…

“ስብስቡ በጣም ደስ ይላል ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁላችንም ከልጅነታችን ጀምሮ የምንመኘው ትልቅ ክለብ ነው። እንደ ትልቅነቱ ሁሉም ነገሩ ደስ የሚል ክለብ መሆኑን አስተውያለሁ በግሌ አሁን ላይ ስመጣ ከገመትኩት በላይ እያየሁት ባለሁት ነገር ደስተኛ ነኝ። ተጫዋቾች ላይ የማየው ስሜት ደስ የሚል ነው ፤ ነባሮቹም ሆነ አዳዲስ የመጣነው ልጆች ውስጥ ዓምና የነበርን ያህል ስሜት ነው ያለው። በአጠቃላይ የቡድኑ መንፈስ ደስ የሚል ነው።”

በመልሶ ጨዋታ ስለሚጠብቀው ነገር…

“እንደ ቡድን ዝቅተኛ ግምት የምንሰጠው ምንም ቡድን የለም ፤ እርግጥ ነው በሜዳቸው ማሸነፍ ችለናል ነገርግን በሜዳችን በቀሪው ዘጠና ደቂቃ ጨዋታውን በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ውጤት በመፈፀም ለደጋፊያችን ደስታን መስጠት እንፈልጋለን።”