የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፣ ጎፈሬ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስምምነት ፈፅመዋል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፓይለት ፕሮጀክት የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፣ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል ዛሬ ከቀትር በኃላ ተፈርሟል።

ከህዳር 2014 ዓ.ም አንስቶ የነገዎቹን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክዋክብቶችን ለማፍራት ታልሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አማካኝነት ከ27 በላይ በሚሆኑ የስልጠና ጣቢያዎች ላይ 970 ወንድ እና ሴት ሰልጣኞች እንዲሁም 135 አሰልጣኞችን ያቀፈው ይህ የታዳጊዎች የፓይለት ፕሮጀክት ዓምና በአርምባንጭ ከተማ እንዲሁም ዘንድሮ ደግሞ በይርጋለም ከተማ የምዘና ውድድሩን እያደረገ ይገኛል።

ታድያ ይህን የምዘና ውድድር ከዓምናው የተሻለ ለማድረግ እና ሰልጣኞችን ለማበረታታት በማሰብ ፌደሬሽኑ ፣ ጎፈሬ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከትጥቅ አቅርቦት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈፅመዋል።

ዛሬ ከቀትር በኃላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው በዚህ የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ አቶ ደረጀ ፉፋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ዋና ፕሬዚዳንት ፣ አቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት እና የጎፈሬ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሳሙኤል መኮንን ተገኝተዋል።

የዛሬው ስምምነት ዓምና ከ15 ዓመት በታች የነበረው ውድድሩ ዘንድሮ ደግሞ ከ16 ዓመት በታች በሚል ለሁለተኛ ጊዜ በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ ካሳለፍነው ማክሰኞ ነሀሴ 16 ጀምሮ እየተደረገ ሲገኝ በውድድሩ የሚሳተፉ ቡድኖች ሁሉም የጎፈሬ ምርት የሆነ ሁለት ዓይነት የመጫወቻ መለያዎችን ጨምሮ የአሰልጣኝ ቡድኖች አባላትን ትጥቆችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ2200 በላይ ትጥቆች የሚቀርቡበት ይሆናል።

የዛሬ መርሃግብርም በሦስቱ አካላት በተወከተሉት ግለሰቦች መካከል በተደረገው የፊርማ ስነ ስርዓት ጅማሮውን ያደረገ ሲሆን አስከትለው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ዋና ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ደረጄ ፉፋ በንግግራቸው ባንኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ በስፖርቱ ዘርፍ የድርሻውን እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን ባንኩ የነገዎቹ ታዳጊዎች በትጥቅ እጥረት ምክንያት ከመንገድ እንዳይቀሩ በማለም የተከወነ የጋራ ስምምነት ስለመሆኑ አንስተዋል።

በማስከተል ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ሲሆኑ እርሳቸውም በንግግራቸው ታዳጊዎች ላይ የመስራት ሀላፊነት በተናጥል ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ብቻ የሚሰጥ አለመሆኑን አንስተው የዛሬው ስምምነት ውጤታማነቱ እየታየ የሚታደስ መሆኑን እና አሁን ባለው ሁኔታ የትጥቅ አቅርቦት ወጪው 70% በባንኩ እንዲሁም ቀሪው 30 % በጎፈሬ የሚሸፈን እንደሆነም አንስተዋል።

በመጨረሻም በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የጎፈሬ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው ትጥቅ ከማቅረብ ባለፈ በቀጣዩቹ ዓመታት በእግር ኳሳችን እድገት ላይ ማነቆ በሆነው የታዳጊዎች ስልጠና ዙርያ ከትጥቅ ጋር ያለውን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ እንደሚሰሩ አንስተው ይህ ስምምነት ለሌሎች መሰል እግር ኳሱን መደገፍ ለሚችሉ ተቋማት ምሳሌ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል።

በመጨረሻም በመርሃግብሩ ከተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው መርሃግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል።