ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል

በግብፁ ክለብ አረብ ኮንትራክተርስ በሙከራ ጊዜ የቆየው ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።

ዮሴፍ ታረቀኝ ወደ ግብፅ በማቅናት ለቀናት በአረብ ኮንትራክተርስ ክለብ ሙከራ በማድረግ ቆይታውን በስኬት ቢያጠናቅቅም ክለቡ በነፃ ዝውውር ዮሴፍን ለመውሰድ ጥያቄ አቅርቦ የተጫዋቹ ህጋዊ ባለቤት የሆነው አዳማ ከተማ የአርባ ሚሊየን ብር የዝውውር ክፍያ መጠየቁ ይታወቃል። አረብ ኮንትራክተርስ ይህን ያህል ብር ለመክፈል እንደሚቸገር በመገለፁ ዝውውሩ ሳይሳካ ቀሮቶ ዮሴፍ ታረቀኝ በዛሬው ዕለት ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።

በአሁን ሰዓት አዳማ ከተማን በመቀላቀል ቡድኑ ባረፈበት ሆቴል የሚገኝ ሲሆን ዮሴፍ ስለቆይታው ሲናገር በነበረው የግብፅ ቆይታ ደስተኛ መሆኑን እና ያገኘው ዕድል ቢሳካ ኖሮ የበለጠ ደስተኛ እንደሚሆን በመግለፅ ሁሉ ነገር ፈጣሪ በፈቀደው እንደሚሆን ተናግሮ ወጣት ተጫዋች በመሆኑ ብዙ ነገር ተምሮ እንደተመለሰ እና በቀጣይ የተሻሉ ዕድሎችን ለማግኘት ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግሯል።