ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፀሐይ ባንክ ጋር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ፈፅመ

👉 “በእውነቱ ፀሐይ ባንክ ከእንቅልፋችን ስለቀሰቀሰን እናመሰግናለን።” አቶ አብነት ገብረመስቀል

👉 “ባንኩ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማገዝ እና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ይሠራል።” አቶ ያሬድ መስፍን

ቀድሞ ከነበረው የፋይናንስ አቅም ጥንካሬ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የገንዘብ እጥረት አጋጥሞት እየተንገዳገደ የሚገኘው አንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህንን ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እየከወነ ይገኛል። በዛሬው ዕለት ደግሞ የፋይናንስ አቅሙን ያሳድጋል የተባለ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ከተመሰረት አንድ ዓመት ካስቆጠረው ከፀሐይ ባንክ ጋር በስካይ ላይት ሆቴል መፈጸም ችሏል። በስነ ስርዓቱም ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኀበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረመስቀል እንዲሁም የፀሐይ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ መስፍን ተገኝተው ውሉን ፈርመዋል።

ከፊርማው በፊት ሁለቱ አካላት ስለ ስምምነቱ ተከታዩን መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል።

በቅድሚያም አቶ አብነት ”አንጋፋው የስፖርት ክለባችን ከፀሐይ ባንክ ጋር ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ፀንቶ የሚቆይ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት የሚፈራረሙበት ቀን በመሆኑ በዚህ ታሪካዊ ቀን በመገኘታችን አመሰግናለሁ።” በማለት “ፀሐይ ባንክ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም ባንኩ በዘመናዊ አደረጃጀት እና ከህዝቡ ጋር ተደራሽነቱን እያሰፋ ባለበት ወቅት የስፖርትን ጠቀሜታነት በመረዳት ከአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተለያዩ የድጋፍ ዓይነቶችን በመፍጠር በአጋርነት ለመሥራት ስለተስማማቹ ከልብ እናመሰግናለን።” ብለዋል።

በመቀጠል የፀሐይ ባንክን በመወከል ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ መስፍን በበኩላቸው “ፀሐይ ባንክ ‘ለሁሉም በሚል’ መሪ ቃል ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን እና ራሱን በህብረተሰቡ ልብ ውስጥ ለማስገባት በርካታ ዘመናዊ ስራዎችን በመሥራት ተደራሽነቱን ማስፋቱን ጠቁመው የአብሮነት እና የወዳጅነት ማጠናከሪያ ፣ የጤናማ ትውልድ ማፍሪያ ፣ የአዕምሮ ማንቂያ የሆነውን የስፖርት ዘርፍ በተግባር ለመደገፍ ከአንጋፋው እና ህዝባዊ መሠረት ካለው ተወዳጁ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር የሚደረገው ስምምነት ተጨባጭ ማስረጃ መሆኑን ተናግረው ባንኩ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማገዝ እና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ የሻምፒዮን/አሸናፊዎች የቁጠባ ሂሳብ ይዞ ብቅ ማለቱን ገልፀዋል።

በማስከተል የተቋሙ ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ የዛሬው በአብሮነት ለመስራት በሚደረገው ስምምነት መጠነ ሰፊ ፋይዳ ያለው ቢሆንም በዋናነት

– የክለቡ ደጋፊዎች የአባልነት ክፍያቸውን በባንኩ በኩል እንዲከፍሉ ይደረጋል።

– ለተጫዋቾቹም ሆነ ሠራተኞች የደሞዝ ሂሳብ በባንካችን በኩል ተከፍቶ ተፈፃሚ ይሆናል።

– የስታዲየም መግቢያ ቲኬቶች እና የክለቡ ቲሸርት በባንኩ ቅርንጫፎች እንዲሸጥ ይደረጋል።

–  ባንካችን በክለቡ የማኀበራዊ ትስስሮች ፣ ጋዜጣ ፣ ሳምንታዊ የሬድዮ መሰናዶ እንዲሁም በተለያዩ የግንኙነት መንገዶች ያስተዋውቃል።

በማለተ ተናግረው በፀሐይ ባንክ በኩል ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገኛቸው የተለያዩ ጥቅሞችን በዝርዝር የተናገሩ ቢሆንም በዋናነት

– ባንኩ በስፖንሰር ሺፕ መልክ በየዓመቱ አስር በመቶ የሚያድግ የአምስት ሚልዮን ብር ለክለቡ ገቢ ያደርጋል።

– ክለቡ የልምምድ ቦታ እና ልማት ግንባታ የሚውል ባንኩ እስከ 40 ሚሊዮን ብር የረጅም ጊዜ ብድር ያመቻቻል ብለዋል።

ከመግቢያ ንግግሩ በመቀጠል በሁለቱ ተቋማት አመራሮች አማካኝነት የስምምነቱ የፊርማ ስነ ስርዓት ከተካሄደ በኋላ ከመገናኛ ብዙኀን ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በዚህ ሂደት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኀበር ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገብረ መስቀል ስለክለቡ ቀጣይ ሁኔታ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል። “ ይህን ስምምነት ለማድረግ ምን ያክል እንደተጓዙ እኛ እና እነርሱ ነን የምናውቀው ። ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የቤት ሥራ የሰጠን ነው። ለምን በእኛ እና በደጋፊዎቻችን ጥረት የምናገኘው ከፍተኛ ገንዘብ ነው። እነዚህን የምናገኛቸው ገንዘቦች ለጥቃቅን ነገር ሳይሆን ወደ ፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰውን ኪስ ሳያይ በልማት ራሱን እንዲችል ለማስቻል ለታቀዱ ዕቅዶች ማስፈፀሚያ እንዲውል ይደረጋል። ሌላው ደግሞ እስከ ዛሬ ይዘን የተኛናቸው ወደ ገንዘብ የሚቀየሩ ብዙ ቦታዎች አሉ። ነገር ግን በራሳችን እና በአሠራራችን ድክመት፣ በተስፋ የሰውን ኪስ እየጠበቅን የሚሄድ ክለብ ነበር። ይሄ ከዚህ በኋላ አያዋጣም ፣ አይተነዋል ተምረናል ሰው ከስህተቱ ተምሮ ተነስቶ የት ይሄዳል የሚለው እንጂ ተሳስቻለው ብሎ ዝም ብሎ እጅና እግሩን አጣጥፎ መቀመጥ የለበትም። ስለዚህ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአሁን በኋላ ከፀሐይ ባንክ ጋር በመሆን በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የረጅም ጊዜ አብረን እየተረዳዳን ክለባችን በሁለት እግሩ እስኪቆም ድረስ አብረን እንሰራለን። በእውነቱ ፀሐይ ባንክ ከእንቅልፋችን ስለቀሰቀሰን እናመሰግናለን”። ብለዋል