የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ዛሬ ሲጀመር በተደረጉ ጨዋታዎች የአቻ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን እና በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ድርጅት ጥምረት የሚዘጋጀው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ዛሬ በተደረጉ የምድብ ሀ ሁለት ጨዋታዎች በይፋ ተጀምሯል። ከቀትር መልስ 07፡00 ሲል የመክፈቻ ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ መካከል ተከናውኗል። ጨዋታውን በክብር እንግድነት በመገኘት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሱ አሩሳ ፣ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ እና የጎፈሬ ትጥቅ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ጨምሮ በርካታ የክብር እንግዶች ተገኝተው ጨዋታውን በይፋ አስጀምረውታል።

ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተቆጠሩ አራት ግቦች ተጠናቋል። ጨዋታው በጀመረ በ4ኛው ደቂቃ ቢኒያም ፍቅሬ ባስቆጠራት ጎል ወላይታ ድቻዎች መሪ መሆን ቢችሉም የጦና ንቦቹ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተከትሎ ጋናዊው አጥቂ ፊሊፕ አጃህ ከዘጠኝ ደቂቃዎች መልስ ሲዳማን አቻ አድርጓል። አጋማሹ ሊገባደድ ሦስት ያህል ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ደስታ ዮሐንስ ከፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን የደረሰውን ኳስ ከመረብ አገናኝቶ ሲዳማን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። ወላይታ ድቻ ተሻሽሎ በቀረበበት በሁለተኛው አጋማሽ 50ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ብዙአየው ሰይፈ ድቻን 2-2 ካደረገ በኋላ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግቦች ሳይቆጠሩ ጨዋታው ተቋጭቷል።

የመጀመሪያው ጨዋታ በጊዜ አለመጠናቀቁን ተከትሎ ዘግየት ብሎ የጀመረው የምድቡ ሌላኛው የፋሲል ከነማ እና የዩጋንዳው ኪያንዳ ቮይስ ጨዋታ በተመሳሳይ ነጥብ በመጋራት ተጠናቋል። ፋሲል ከነማዎች ሻል ብለው በታዩበት 20 ደቂቃዎች ውስጥ ጌታነህ ከበደ 10ኛው ደቂቃ ላይ በግል ጥረቱ ከተከላካይ የነጠቀውን ኳስ ግብ አድርጎ ፋሲልን ቀዳሚ አድርጓል። ራሳቸውን ከዕረፍት መልስ አሻሽለው ከተመለሱ በኋላ ፋሲሎችን በእጅጉ የፈተኑት ኪያንዳ ቦይሶች 64ኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠውን አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት ተከላካዩ ማቱቩ ሱላ አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ 1-1 ተለውጧል። ከ80 ደቂቃዎች በኋላ በሜዳ ላይ ጭቅጭቆች እና ውዝግዞች በመስተዋላቸው በፋሲል በኩል ምኞት ደበበ በቀይ ካርድ ወጥቷል። ጨዋታውም በመጨረሻ አንድ አቻ ተደምድሟል።

ጨዋታው በነገው ዕለትም በምድብ ለ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል።