ነገ የሚደረገው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በኢትዮጵያዊያን ዳኞች ይመራል

በነገው ዕለት ቱኒዚያ ላይ የሚደረገውን የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ይመሩታል።

የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2023/24 የውድድር ዘመን የማጣሪያ ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት መደረግ መጀመራቸው ይታወሳል። በነገው ዕለት የሊቪያው ክለብ አሀሊ ቤንጋዚ ከአይቮሪኮስቱ አሴክ ሚሞሳ የሚያደርጉትን ጨዋታ ደግሞ አራት ኢትዮጵያን ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲመሩ መመረጣቸውን ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ ይጠቁማል።

ሊቢያ ላይ እስከ አሁን ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በቱኒዚያ ራባት ስታድ ኦሎምፒክ ዲ ሶስ ስታዲየም ላይ ነገ ሰኞ አመሻሽ 11፡30 ሲል የሚደረገውን ይህን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ቴዎድሮስ ምትኩ ሲመራው ትግል ግዛው እና ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ ጨዋታ የተመረጠው ሙስጠፋ መኪ በረዳት ዳኝነት ሲያገለግሉ በላይ ታደሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ከስፍራው ደርሰዋል። ጨዋታውን በኮሚሽነርነት ለመታዘብ አሚን ሞጉ ከቱኒዚያ ተመርጠዋል።