ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ በሀብታሙ ታደሰ ግቦች ክለብ አፍሪካን ረተዋል

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታ የቱኒዚያውን ክለብ አፍሪካን የገጠሙት ባህርዳር ከተማዎች በሀብታሙ ታደሰ ግቦች 2-0 መርታት ችለዋል።

9፡30 ላይ በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ባህርዳር ከተማዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ችለው ነበር። ቸርነት ጉግሣ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት በመግባት የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሲያባክነው በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ አለልኝ አዘነ ከፍሬው ሰለሞን በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ሀሰን ሙኤዝ መልሶበታል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በቀጥተኛ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት ክለብ አፍሪካኖች የመጀመሪያ ሙከራቸውን 11ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። በዚህም ባሲም ስራርፊ በጥሩ ሁኔታ ገፍቶ በወሰደው ኳስ ከቀኝ መስመር ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይዞበታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ መሀመድ ጋኢዝ ከቅጣት ምት ያደረገው ጥሩ ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ይበልጥ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ በሁለቱም በኩል የሚቆራረጡ ኳሶች የሚታዩበት ነበር። ሆኖም 35ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ውሳኔዎች ግሩም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ፍሬዘር ካሳ አሊ አምሪ ላይ ከሳጥን አጠገብ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት መሀመድ ጋኢዝ በድንቅ ሁኔታ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት ክለብ አፍሪካኖች 44ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ኢዱዎ ኪንግስሊ  አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው መሀመድ አሚን ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ በተጨመሩ 6 የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት የጣና ሞገዶች 45+3′ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከግራ መስመር የተነሳውን ኳስ ፍጹም ጥላሁን ሙሉ በሙሉ ሳያገኘው ቀርቶ ተከላካዮች ተደርበው የመለሱትን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ሀብታሙ ታደሰ መረቡ ላይ አሳርፎታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ክለብ አፍሪካኖች ወደ ባህርዳር ከተማ የግብ ክልል በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመግባት በመሀመድ ጋኢዝ ሊፈጥሩት የነበረውን የግብ ዕድል ያሬድ ባዬህ በግሩም ቦታ አያያዝ አምክኖባቸዋል።

ከዕረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ስኬታማ ቅብብሎች ይደረጉ እንጂ የጠሩ የግብ ዕድሎች በርከት ብለው ባለመፈጠራቸው ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሲሄድ 58ኛው ደቂቃ ላይ ፍጹም ጥላሁን ከሳጥን ውጪ ያደረገው እና ግብ ጠባቂው ሀዘን ሙዔዝ የመለሰው ሙከራ የአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ጨዋታው 74ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ክለብ አፍሪካኖች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሆኖም አሊ አምሪ ከረጅም ርቀት በተሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ ኳሱን ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም በጣና ሞገዶቹ በኩል ተቀይሮ የገባው ዱሬሳ ሹቢሳ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መልሶበታል።


ከመሃል በሚሰነጠቁ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት ክለብ አፍሪካኖች 84ኛው ደቂቃ ላይም በድጋሚ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበት ዕድል ፈጥረው ነበር። ሆኖም ተቀይሮ የገባው ሀምዲ አቢዲ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም በዕለቱ ኮከብ የነበረው ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍና አግዶበታል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ 90ኛው ደቂቃ ላይ ክለብ አፍሪካኖች የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ተሠርቶብናል ብለው ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረቡ በነበረበት አጋጣሚ በግራ መስመር ኳሱን እየገፋ የወሰደው ዱሬሳ ሹቢሳ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ግብ ሆኗል። ከግቧ መቆጠር በኋላም ክለብ አፍሪካኖች እጅግ ከፍተኛ ቅሬታ ማሰማታቸውን ቀጥለው ጨዋታውም በባህርዳር ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።