ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ | ሀዋሳ እና መቻል ድል ቀንቷቸዋል

በሁለተኛ ቀን የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታ ሀዋሳ እና መቻል ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ለ የሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው በመሸናነፍ ተጠናቀዋል። ቀደም ብሎ ሀዋሳ ከተማን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን አስመልክቶን በሀዋሳ አሸናፊነት ተጠናቋል። ረጃጅም ኳሶችን ሀዋሳ ከተማዎች የመስመር አጨዋወትን ወልቂጤ ከተማዎች ባዘወተሩበት የመጀመሪያው አጋማሽ 44ኛው ደቂቃ ላይ ተባረክ ሄፋሞ ከቀኝ ወደ ውስጥ ለዓሊ ሱለይማን ሲያቀብለው ተሸራርፋ የደረሰውን ኳስ እዮብ አለማየሁ በግንባር ገጭቶ ሀዋሳን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ መልክን ተላብሶ በቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ወልቂጤዎች በርከት ያሉ ለውጦችን በማድረግ በይበልጥ ወደ ጨዋታ መግባት ቢችሉም የፊት አጥቂዎቻቸው የስልነት መሳሳት ይታይባቸው ስለነበር ጎሎችን በቀላሉ ከመረብ ሊያገናኙ አልቻሉም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ከወልቂጤ በኩል ጌቱ ሀይለማርያም በሳጥኑ ጫፍ ቸርነት አውሽ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ጨዋታውም በሀዋሳ 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

በመቀጠል መቻልን ከድሬዳዋ ከተማ 09፡00 ሲል ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ መርሀግብር መቻሎች በሁለት አጋማሾች ከመረብ ባሳረፏቸው ግቦች ታግዘው ድል ቀንቶቸዋል። ጨዋታውን የዕለቱ ዳኛ ባስጀመሩበት ቅፅበት 1ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከቀኝ ወደ መስመር ካደላ ረጅም ቦታ ላይ አክርሮ በመምታት የአብዩ ካሳዬ የጎል አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ኳሷ መረብ ላይ አርፋ መቻል ቀዳሚ ሆነዋል።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ለውጥን ጭምር አድርገው ሜዳ ላይ ቢቀርቡም በቀላሉ ኳስ እና መረብ ለማገናኘት ጥድፊያ ውስጥ መገኘታቸውን በጨዋታው አስተውለናል። ይሁን እና 81ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ በሀዋሳ በክረምት ወር በተደረገው የሰመር ካፕ ጨዋታ ላይ የተገኘው ሙሀባ አደም ተቀይሮ ከገባ በኋላ ሜዳ ላይ በፈጠረው ጥሩ እንቅስቃሴ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በመጨረሻም በመቻል 2ለ0 ተደምድሟል።

ውድድሩ የምድብ ሀ ሁለተኛ ጨዋታዎችን በነገው ዕለት ሲያስተናግድ ሲዳማ ቡና ከ ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን ከ ኪያንዳ ቦይስ ያገናኛል።