አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የኢትዮጵያዊቷን አሰልጣኝ የመጀመሪያ ጨዋታ ይመራሉ

አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የሚመራው የላይቤሪያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ።

በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የ2024 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ሀገራት የማጣሪያ መርሀግብራቸውን ከሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ጀምረው ማከናወን ይጀምራሉ። በዚህ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያዊቷን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት ላይቤሪያዎች ወደ ፕራአያ ተጉዘው ኬፕ ቨርዲን ሲገጥሙ አራት ኢትዮጵያውያን ዳኞች ጨዋታውን እንዲመሩ ስለመመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የፊታችን ዕርብ ምሽት 2፡00 የኬፕቨርዲ ዋና ከተማ በሆነችው ፕራአያ ከተማ በሚገኘው ስታዲዮ ናሲዮናል የሚደረገው ኢትዮጵያዊያኑን ያገጣጠመውን ይህን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት መዳብ ወንድሙ ስትመራው በረዳት ዳኝነት ወጋየሁ ዘውዴ እና ብርቱካን ማሞ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ሲሳይ ራያ በጣምራ በጋራ ይህን ጨዋታ ይዳኛሉ።