ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ | ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ከምድባቸው አልፈዋል

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ወላይታ ድቻ ፋሲል ከነማን ፣ ሲዳማ ቡና ኪያንዳ ቦይስን በመርታት ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

በሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን እና በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ድርጅት በጋራ በመሆን የተሰናዳው ሁለተኛው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታ የምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ከቀትር መልስ በተመሳሳይ ሰዓት ሲደረጉ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ከምድባቸው ማለፋቸው ታውቋል።

 

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ወላይታ ድቻን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው መርሀግብር? በመጨረሻም ድቻን አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል። ጥሩ ፉክክሮችን ባስተዋልንበት እና ወላይታ ድቻ አንፃራዊ የተሻለ እንቅስቃሴን ባሳየበት ጨዋታ ቢኒያም ፍቅሬ በጨዋታ ፍፁም ግርማ ከቅጣት ምት ለድቻ ግቦቹን ሲያስቆጥሩ አማካዩ ኤልያስ ማሞ ከሽንፈት ፋሲልን ያላዳነች ብቸኛ ግብ አክሏል። ጨዋታው 2ለ1 በሆነ ውጤት የድቻ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ምድቡን በ7 ነጥብ መሪ ሆኖ እንዲፈፅም አስችሏል።

በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ሲዳማ ቡናን ከዩጋንዳው ኪንዳ ቦይስ ያገናኘው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ግማሽ ደርዘን ጎሎችን በማስቆጠር ወደ ቀጣዩ ዙር ሁለተኛ ሆኖ ማለፉን አረጋግጧል። በጨዋታው ሙሉ በሙሉ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ከዕረፍት በፊት እና በኋላ ይገዙ ቦጋለ እና ጋናዊው አጥቂ ፊሊፕ አጃህ አራቱን ግቦች ለክለቡ ሲያስቆጥሩ አዲስ ፈራሚው በዛብህ መለዮ እና በጭማሪ የጨዋታ መጠናቀቂያ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ ለቡድኑ ግቦችን ከመረብ ያሳረፉ ተጫዋቾች ሆነዋል። ሜዲ ካይኡኔ የኪንዳ ቦይስን ብቸኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሲዳማ 6ለ1 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።