ሊዲያ ታፈሰ ከሦስት የሀገሯ ዳኞች ጋር በአፍሪካ መድረክ የመጨረሻ ጨዋታዋን ታከናውናለች

ሎሜ ላይ ጅቡቲ ከቶጎ የሚያደርጉትን የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን አራት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ሲመሩት ሊዲያ ታፈሰም የመጨረሻ ጨዋታዋን በዳኝነት ትሳተፋለች።

የ2024 የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ጨዋታ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይከናወናል። ሀገራት በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ለመሆን በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን ጅቡቲን ከቶጎ የሚያገናኘውን ጨዋታ አራት እንስት ኢትዮጵያውያን ዳኞች እንዲመሩት ስለመመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ የደረሳት መረጃ ያመላክታል። በትላንትናው ዘገባችን ሌሎች አራት ኢትዮጵያውያን ዳኞች የኬፕቨርዲ እና ላይቬሪያን ጨዋታን እንደሚመሩ በዘገባችን ጠቁመን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ሌሎች አራት የሀገራችን ዳኞች ቶጎ ሎሜ ደርሰዋል።

ጅቡቲ ሜዳዋ የካፍን መመዘኛ አለማለፉን ተከትሎ የደርሶ መልስ ጨዋታዋን በተጋጣሚዋ ሀገር ቶጎ የምታደርግ ሲሆን በነገው ዕለት ዕርብ ምሽት 12፡30 ላይ በስታድ ዲ ኬጉ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ይከናወናል። ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ፀሀይ አበበ ፣ በረዳት ዳኝነት ወይንሸት አበራ እና ይልፋሸዋ አየለ ሲመሩት በቅርቡ ከዳኝነት ራሷን ያገለለችው እና የዳኞች ኢንስትራክተር የሆነችው ሊዲያ ታፈሰ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ የፊፋ የዳኝነት ባጅ ስላላት ካፍ ይህን ጨዋታ በአራተኛ ዳኝነት እንድታገለግል ጥሪ በማቅረቡ አብራቸው በዳኝነት የአፍሪካ መድረክ የመጨረሻ ጨዋታዋን ትመራለች።