አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የብሔራዊ ቡደን ቆይታቸውን ሊያራዝሙ ነው

ያለፉትን አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ያሰለጥኑት ፍሬው ኃይለገብርኤል ለተጨማሪ አመት እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

በ2024 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ነገ ከቡሩንዲ አቻው ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ የቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሶከር ኢትዮጵያም ዋና አሰልጣኙ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚኖራቸው የውል ዘመን እየተጠናቀቀ መሆኑን ተከትሎ በቀጣይ ቆይታቸው ዙርያ ላቀረበችው ጥያቄ አሰልጣኙ በምላሻቸው “ የውል ዘመኔ መጠናቀቁን ተከትሎ የተከበሩ የፌዴሬችኑ ስራ አስፈፃሚዎች አክብረው ጠርተውኝ ያለኝን ቀጣይ ዕቅድ አቅርቤ ተነጋግሬያለው። እነርሱም ከዚህ ቀደም ለሰራሁት ስራ ዕውቅና በመስጠት ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ለመቆየት ተስማማምቼ ወጥቻለው። ከዚህ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁሉም ነገር መፍትሄ ያገኛል”። ብለዋል