ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ | የምድብ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተጠናቀዋል

የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ሀዋሳ እና መቻል ማለፋቸውን ያረጋገጡበትን ውጤት ሲያስመዘግቡ ድሬዳዋም ድል ቀንቶታል።

ክለቦች ከዋናው የሊግ ውድድራቸው በፊት ራሳቸውን የሚለኩበት የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የምድብ ሁለት መርሀግብር በተመሳሳይ ሰዓት በሁለት ሜዳዎች ላይ በዛሬው ዕለት ተደርገው ሲጠናቀቁ አላፊ ክለቦች ተለይተውበታል። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ ቀደም ብሎ ምድቡን መሻገር የቻለውን ሀዋሳ ከተማን ከ መቻል ያገናኘው ጨዋታ ተከናውኗል። ጥሩ ፉክክሮችን ሜዳ ላይ ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መቻሎች በአመዛኙ መሐል ሜዳውን በመጠቀም በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች በሚሻገሩ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት ጥረቶች ቢያደርጉም ጨዋታው ያለ ጎል ፍፃሜውን አግኝቷል።

በአርቴፊሻል ሜዳ ላይ ድሬዳዋ ከተማን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኘው ሌላኛው ጨዋታ ድሬዳዋን አሸናፊ አድርጓል። ዩጋንዳዊው አጥቂ ቻርለስ ሙሴጌ በጨዋታ ዳዊት እስጢፋኖስ በፍፁም ቅጣት ምት ለድሬዳዋ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ ለሁለቱ ጎሎች መገኘት የካርሎስ ዳምጠው ድርሻ ከፍ ያለ ነበር። ወልቂጤን ከሽንፈት ያላዳነች ብቸኛ ግብም ሔኖክ ኢሳያስ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።