ነገ ከሚካሄደው የቡሩንዲ ጨዋታ አስቀድሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል

👉 “ዕቅዳችን የአፍሪካ ዋንጫ መግባት ነው…”

👉   “ለሚወዷት ሀገር ታማኝ የሆኑ ናቸው…”

👉   “በሜዳ ውስጥ ተጫዋቾች የተለየ አቋም አውጥተው መጫወት ካልቻሉ…”

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከቡሩንዲ አቻው ጋር ለሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ የዝግጅት ጊዜው እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ዛሬ በፌዴሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለሚዲያ አካላት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በመግቢያ ንግግራቸው እንደተናገሩት ዝግጅት ከጀመሩ አስራ ሁለት ቀናት እንደሆናቸው እና የተጫዋቾቹን አቋም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ብዙ ሂደቶች እንደሄዱ ተናግረው ከልምምድ ሜዳ ጋር ተያይዞ ተግዳሮቶች እንደገጠሟቸው አውስተዋል። ሁለት ዓይነት መልክ ያለው ስብስብ እንደነበራቸው በዚህም አንደኛው በሴካፋ የአፍሪካ ክለቦች ዋንጫ ተሳትፎ አድርጎ ከጨዋታ የመጣ ስብስብ ሌላኛው ደግሞ ከጨዋታ ውጭ አርፈው የመጡ ተጫዋቾች የነበሩ ቢሆንም ሁለቱን አቻችሎ ለማስኬድ በሚችሉት አቅም ለጨዋታው ለማድረስ ጥረት ማድረጋቸውን እና አጠቃላይ ያለው ነገር አመርቂ መሆኑን ገልፀዋል።

በማስከተል የተለያዩ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች የቀረቡ ሲሆን በዋናነት በተነሱ ጥያቄዎች እና በምላሾቹ ዙርያ የሰጡትን ሀሳብ በተከታይነት አቅርበነዋል።

ስለ ዝግጅታቸው…

የአፍሪካ ዋንጫውን ያማከለ ዝግጅት አድርገሃል ብትሉኝ አላደረኩም። ለምን የሜዳ ችግር ፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ለዝግጅት ያገኘሁበት ጊዜ አስራ ሁለት ቀን ነው። ከጨዋታ ርቀው ለመጡ ተጫዋቾች ብዙ ቀን ነው ብዬ አላስብም። ግን ምንድን ነው በተቀመጠው ሳይንስ መሰረት በዚህ ቀን ውስጥ እንዴት ቡድን ሠርቶ ለጨዋታ ማቅረብ እንደሚቻል ስለማውቅ በዚህ መልኩ ሠርቻለው። ይህን ስል ቀኑ አንሷል ብዬ ቅሬታ እና ሰበብ በማቅረብ ለመሸሽ ሳይሆን ቡድን ለመገንባት ከባድ መሆኑን ለመግለፅ ነው። ጊዜው አጥሯል አዎ አጥሯል ለዚህ የአፍሪካ ዋንጫ የተሟላ ዝግጅት አድርገሃል ነው አላደረኩም ነው መልሴ።

ዘለግ ላለ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን ስለ መቆየታቸው ጠቀሜታ…

በአንድ ቡድን ተጫዋቾች ረዘም ላለጊዜ አብረው መቆየቱ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። አሰልጣኝም እንደዛው ነው። ሙያውን በጥሩ ለማውጣት የቆይታ ጊዜ ብዙ ቢሰጠው ይጠቅማል። ይሄ ደግሞ ሆኗል ስቀጠር የመጣሁት ከ20 ዓመት በታች ቡድን ለማሰልጠን ነው። በዚህም ወደ አራት ዓመት ሆኖኛል በዚህ ቆይታ ውስጥ ግን ዋንጫ ማምጣት ብቻ ትኩረት መደረግ አለበት ብዬ አላምንም። ከዋንጫው ጀርባ ለኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምን ያህል ግብዓት የሆኑ ተጫዋቾችን አምጥቻለው የሚለው ነው። አሁን ባለው ብሔራዊ ቡድን ከሎዛ ፣ ከታሪኳ በርገና፣ ቅድስት እና ከሴናፍ ዋቁማ ውጭ ሌሎቹ አብዛኛው ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ናቸው። ሌላው ከ18 ዓመት በታች ቡድን አራት ልጆች አሉ ስለዚህ ቡድኑ እየተቀናጀ ነው። በቀጣይ ሰፊ ጊዜዎችን የማገኝ ከሆነ በአፍሪካ ዋንጫ፣ በዓለም ዋንጫ የሚገባ ቡድን ለመሥራት ምንም ጥርጥር የሌለው ሥራ ይሠራል ብዬ አስባለሁ።


የአፍሪካ ዋንጫ ስለመግባት የታቀደው ዕቅድ…

አስራ ሁለት ቀን ቡድን አዘጋጅቼ አሁን ላይ የአፍሪካ ዋንጫ እገባለው ብሎ መናገሩ ከሙያ አኳያ ደፍሮ መናገር አያስችልም ብዬ አስባለው። ግን ዕቅዳችን(ሀሳባችን) የአፍሪካ ዋንጫ መግባት ነው። በቀጣይ ባሉን ጊዜያት በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ቡድኑን እያስተካከልን ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማንገባበት ምክንያት የለም። ሁላችንም ትኩረት አድርገን እየሠራን ያለነው በእርግጠኝነት የአፍሪካ ዋንጫ ለመግባት ነው። አሁን ያለው ትውልድ ይዞት የተነሳው ዓላማ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መግባት ነው። እጅግ ስርዓት ያላቸው፣ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ አሰልጣኛቸውን የሚያከብሩ ፣ ለሚወዷት ሀገር ታማኝ የሆኑ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ልጆቹን አመሠግናለሁ። ጥሩ ውጤት ያስመዘግባሉ ብዬም አስባለሁ።

የደርሶ መልሱ ጨዋታ በሜዳቹ መሆኑ ያለው ጠቀሜታ…

በዘመናዊ እግርኳስ የሜዳ ላይ ጨዋታን አሸንፎ ውጤት አመጣለው ማለት ከባድ ነው። ኳሷም፣ ጎሉም ሜዳውም ለሁለታችንም እኩል ነው። ምናልባት የአየር ንብረት ለውጥ ካላመጣ በቀር በሜዳ ውስጥ ተጫዋቾች የተለየ አቋም አውጥተው መጫወት ካልቻሉ በስተቀር በሜዳችን በመጫወታችን ብቻ ውጤት ይመጣል ብሎ መጠበቅ የማይሆን ነገር ነው። ዋናው ነገር የሜዳ ጥቅም ሆነን እና መሥራት ስንችል ብቻ መሆኑን አስረድተናቸዋል።