የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-1 ኢትዮጵያ መድን

“ከመመራት ከመነሳታችን አንፃር ብዙ አልከፋኝም” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

“ብዙ ነገሮችን ተቋቁመን ይሄንን ውጤት ይዘን ወጥተናል” አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ

የሊጉ 12ኛ ጨዋታ በፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን መካከል ተከናውኖ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ከተጋጣሚ አሰልጣኞች ጋር ተከተዩን ቆይታ አድርገናል።

“አሰልጣኝ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለጨዋታው

” ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነው። በተለይ ከዕረፍት በፊት በመከላከል አደረጃጀት በኩል ክፍተቶች ነበሩብን ፤ በተለይ በረጅሙ የሚመጡ ኳሶችን መቆጣጠር ላይ። ከዕረፍት በኋላ ግን ጥሩ ነበርን ማለት ይቻላል። ጥሩ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃትም ዕድሎች ነበሩን። በአጠቃላይ ቡድን ቀስ እያለ ስለሆነ የሚሄደው መጥፎ አይደለም።”

ከናትናኤል እና ቃልኪዳን ቅያሪ በኋላ ቡድኑ እንዳሳየው አቋም ውጤቱ ሲታይ…

“በእርግጥ ቅድሚያ መመልከት ያለብን እንቅስቃሴውን በምን ደረጃ ይዘን እየሄድን ነው የሚለውን ነው። ረጅም ውድድር ስለሆነ በማንኛውም ሁኔታ ነጥብ ልታገኝም ልታጣም ትችላለህ። ሁለቱ ልጆች ከገቡ በኋላ ለቡድኑ የሰጡት ተጨማሪ ጉልበት አለ። ከዛ በላይ ግን የኋላ መስመራችን መረጋጋቱ  እና በመጀመሪያው አጋማሽ ይመጡ የነበሩ እና የተቸገርንባቸውን ረጅም ኳሶች የራሳችን አድርገን መጫወታችን የበለጠ እንድናጠቃ አድርጎናል። ከመመራት ከመነሳታችን አንፃር ብዙ አልከፋኝም።”

በግራ መስመር ስለ ኢዮብ ማቲያስ ማጥቃት መገደብ…

“ኢዮብ የጨዋታ ዝግጁነቱ ገና ነው። ሁለተኛ የመድን ጠንካራ የማጥቃት ክፍል በእነሱ የቀኝ መስመር የሚነሱ ናቸው ፤ ቀደም ባሉ ጨዋታዎች ላይ እንደተመለከትነው። ያንን ከመቆጣጠር አንፃር ነው። ከዕረፍት በኋላ ግን በርካታ ጊዜ ወደፊት ሄዷል ቡድኑን በደንብ አግዟል።”

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለጨዋታው…

“ጥሩ ነው ፤ እንዳሰብነው ነው። ፍጥነቱን ጨመር አድርገን አስፈላጊውን ነገር ማግኘት እንድንችል ነበር። ልጆቹ በዛ ፍጥነት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት በጣም ጥሩ ነው። ያው የተወሰኑ ስህተቶች ይኖሩብናል። ግን እንደነበረው ሁኔታ ማሸነፍ ይገባን ነበር። በተለይ አንድ ያለቀለት ኳስ ስተናል። ግን ጥሩ ነው በዚህ ዕድሜ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ይህን ጥረት እና ጨዋታ ማሳየታቸው ጥሩ ነው።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስላሳዩት መቀዛቀዝ…

“አንድ ጎል አግብተን ነበር። በራሱ የሚመጣ ነገር ይኖራል ፤ ያንን ጠብቆ የመውጣት ዓይነት። ውስጡ ያው በሥነልቦና ተጫዋቾች ላይ የሚፈጥረው ጫና አለ። ያ እንዳይፈጠር ዕረፍት ላይ ነግሬያቸዋለው ፤ እንደገና መልሰን ማጥቃት እንዳለብን ማለት ነው። ነገር ግን እነሱም የሚችሉትን ማድረግ ነበረባቸው እና እኛ ላይ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል። ሆኖም ብዙ ነገሮችን ተቋቁመን ይሄንን ውጤት ይዘን ልንወጣ ችለናል ፤ ብቻ ውጤቱ መጥፎ አይደለም።”