የሊጉ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የቀን ማሻሻያ ሲደርግባቸው የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭትም አያገኙም።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ ላይ እየተደረገ ሦስተኛ ሳምንት መርሀግብር ላይ ደርሷል። የመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ካገኙ በኋላ ከሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ አሁኑ የሦስተኛ ሳምንት ድረስ ሽፋኝ እያገኙ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሲሆን የሊግ አክሲዮን ማህበሩ ባጋራው መረጃ መሠረት ቀጣዮቹ የአራተኛ እና የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጨዋታዎች ስላሉት የዝግጅት ጊዜዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጨዋታዎቹ ላይ የቀን ሽግሽግ ተደርጎባቸዋል። በዚህም መሠረት ቀጣይ ሳምንት ጥቅምት 15 የሚጀምረው የ4ኛ ሳምንት ጨዋታ አንድ ቀን ወደ ኋላ ተስቦ ጥቅምት 14 ሲጀመር የ5ኛ ሳምንት ጨዋታ መጀመሪያ ቀንም ከጥቅምት 22 ወደ ጥቅምት 20 ተለውጧል።

በተጨማሪም የእነኚህ የአራተኛ እና የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደማይኖራቸውም ተገልጿል።