የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀድያ ሆሰዕና 0-0 ወልቂጤ ከተማ

“ውጤቱ አስፈላጊ ስለነበረ ለመሸናነፍ የነበረው ነገር ጥሩ ነው ፣ ያሰብነው ግን አላሳካንም” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት

“ጫና እኮ ራስህ የምትፈጥረው ነው ፣ የምትሸከመው ነገር አይደለም ፣ ይሄ መቶ ኪሎ ጤፍ አይደለም” አሰልጣኝ የሐንስ ሳህሌ

ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የዕለቱ ቀዳሚ የሀድያ እና ወልቂጤ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል።

አሰልጣኝ የሐንስ ሳህሌ – ሀድያ ሆሳዕና

ስለ ጨዋታው …

“ተመጣጣኝ ነበረ ማለት እንችላለን ፣ በብዛት ጨዋታው የነበረው መሐል ሜዳ ላይ ነው ብዙ የጎል ዕድሎች የተገኙበት አይደለም። ያገኘነውንም አልተጠቀምንም እነርሱም አንድ አግኝተው ነበር አልተጠቀሙም። ከዛ ውጪ ግን ብዙ ሽኩቻ የነበረበት ነበር ፣ መሐል ሜዳ አካባቢ እና እነርሱም ካሉበት ለመውጣት እኛም ካለንበት ለመውጣት የተደረገ የጨዋታ አይነት ነው የሚመስለው ፣ የሁለታችንም አካሄድ አንድ ዓይነት ነበር ማለት ይቻላል እነርሱም ትንሽ ይመጣሉ ፣ እኛም ትንሽ እንሄዳለን የመፈራራት ነገርም ነበር ፣ ግን ብዙ የጎል ሙከራዎች ያልተደረጉበት ጨዋታ ነበር። መሐል ሜዳ ላይ በተቆራረጡ ኳሶች ያለቀ ዓይነት ጨዋታ ይመስል ነበር።”


ውጤት ከማጣት አንፃር ስለ ሚኖረው የስነ ልቦና ጫና…

“ገና እኮ ነው ጨዋታው ፣ የስነ ልቦና ችግር ምንም ጊዜ አለ ፣ እየመራህም ከሆነ ላለመሸነፍ ስነ ልቦና አለ ፣ እያሸነፍክም ቢሆን ሁለት ጨዋታም ተጫውተህ ተሸንፈህ ስነ ልቦና አለ። ትልቁ ነጥብ ምንድነው እያንዳንዱን ጨዋታ እንደ አመጣጡ ነው እንጂ መቀበል ያለብህ ያለፉትን ጨዋታዎች እየቆጠርክ ከሆነ የስነ ልቦና ችግር ሊኖርብህ ይችላል። ጫና እኮ ራስህ የምትፈጥረው ነው ፣ የምትሸከመው ነገር አይደለም ፣ ይሄ መቶ ኪሎ ጤፍ አይደለም ፣ ራስህ የምትፈጥረው ነው ችግር ውስጥ ከሆንክ ከችግር ለመውጣት ፖዘቲቭ ማሰብ ነው የሚገባህ ፣ ጥሩ ነገር ላይ ከሆንክ ደግሞ ያን ጥሩ ነገር አስቀጥላለሁ ብለህ ነው እንጂ ፣ ያለፈን ነገር ይዘህ የምትመጣ ከሆነ ራሱ ለመጫወትም ሆነ ለተመልካቹም የሰራህውን ተግባራዊ ለማድረግ ትቸገራለህ።”

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች…

“መከላከል ላይ ጥሩ ነን ፣ ማስጠበቅ ላይ ጥሩ ነን ፣ ዛሬ አንድም ኳስ በረኛችን አልያዘም ፣ የባንክ ጨዋታም ላይ አንድም ኳስ አልያዘም ራሳችን ላይ ካገባነው ውጪ ፣ የመከላከያም ዕለት ሁለት ጊዜ መተው ነው ሁለቱንም ያገቡብን ፣ ስለዚህ አዲስ ቡድንም ቢሆን ምክንያት መደርደር አያስፈልግም። አዲስ ነው ብለህ የምናሰልፋቸው ልጆች በብዛት አዲስ ናቸው ለእዚህ ክለብ እኔም አዲስ ነኝ ግን በእግር ኳስ የቆየን ከሆንን ደግሞ አንዳንድ ነገሮችን ሜዳው ላይ የራሳችንን ተጫዋቾች ማስተካከል የሚገባንን ማስተካከል መቻል አለብን። አዲስ ነው ተብሎ ብቻ ምክንያት መፍጠር አያስፈልግም። ከዛ አንፃር ስትመለከተው አዎ የመግባባት አንዳንድ ጊዜ የሚቆራረጡ ኳሶች ፣ በዚህ ላይ ጉዳት ይመጣና ተጫዋቾች ሲወጡብህ አዲስ ሰው ሲገባ እነርሱን ደግሞ አንድ ላይ ለማቀናጀት ችግር ነው ግን በመከላከል ደረጃ ጥሩ ነን በደንብ ሰርተናል ፣ ፊት ላይ በደንብ መስራት አለብን የኋላውን ሳንረሳ።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ሁለቱ አጋማሾች…

“ጥሩ ነው የመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ የበላይነት ቢኖረንም መጠቀም አለመቻላችን አየሩ ትንሽ አድቫንቴጆች አሉት ፣ ሁለተኛው አርባ አምስት ደግሞ የፈለግነው ጎል ነበር ፣ እንደዛም ሆኖ ትንሽ ጥብቅ ስለነበረ በእኛም በእነርሱም በኩል ውጤቱ አስፈላጊ ስለነበረ ለመሸናነፍ የነበረው ነገር ጥሩ ነው ፣ ያሰብነው ግን አላሳካንም።”


ካለፈው ጨዋታ አንፃር ዛሬ የሰሩት የተለየ ነገር …

“አቻ ነው የወጣነው ጥሩ ነው ፣ አሁንም በተመሳሳይ አቻ ነው ፣ ቢሆንም ተፅዕኖዎች አሉት ዘጠኝ ሰዓት ተደጋጋሚ ሦስት ጨዋታ በመጫወታችን ትንሽ ፀሀዩ ከባድ ነው ፣ ድካምም ስላለው ከቀን ወደ ቀን ትንሽ ተጫዋቾቼ ላይ ድካም ይታያል። የከፈሉት ዋጋ ግን በሦስቱም ቀን እጅግ በጣም ደስ ይል ነበር እና ያላቸውን ነገር እያወጡ እየሰጡ ነውና ፣ ከዚህ በኋላ አጭር ጊዜ እንደ መጀመራችን በስቴፕ የተሻለውን ወልቂጤ ለመስራት ነው እየሄድን ያለነው።”

ካለው የኳስ ቁጥጥር አኳያ ስለሳሳው ማጥቃት…

“በዕርግጥ ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት ተጫዋቾቹ የሚመቹ ናቸው ፣ ጥሩ ናቸው ተደጋጋሚ ያው መስራት ነው።ያለቁ ኳሶች አግኝተናል ግን እዚህ ላይ መስራት ነው ፣ ሁሌም አጥቂዎቹም የራሳቸው የሆነ የአጨራረስ ስራዎች በግላቸው ከልምምድ ውጪ ራሳቸውን ለግብ የሚሆኑ ቦታ አያያዞን በደንብ ልምድ ያላቸው ስለሆኑ ከእነርሱ የሚጠበቅ ነው። እኛ ግን እንደ አሰልጣኝ በአጠቃላይ የቡድኑ የግብ ማግባት ችግር ስለሆነ ተደጋጋሚ ሁሌም መስራት ነው ያለብን”