ሪፖርት | ነብሮቹ እና ሠራተኞቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ሀዲያ ሆሳዕናን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ያለ ግብ ተጠናቋል።

የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሁለቱን ድል ያላደረጉትን ሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማን ሲያገናኝ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ካለፈው የንግድ ባልክ ሽንፈት አንፃር በሦስቱ ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል። ዘካሪያስ ፍቅሬ ፣ ተመስገን ብርሀኑ እና ዳዋ ሆቴሳ አርፈው ሔኖክ አርፊጮ ፣ ሠመረ ሀፍታይ እና ግርማ በቀለ ሲተኳቸው በወልቂጤ በኩል በተደረገ ብቸኛ ለውጥ ጉዳት በገጠመው አቡበከር ሳኒ ቦታ ተመስገን በጅሮንድ ተተክቷል።

9፡00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በጀመረው ጨዋታ ወልቂጤዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው አሜ መሐመድን መነሻ ባደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ሲሞክሩ በመጀመሪያ ጥቂት ደቂቃዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት ሀዲያዎች የሚያገኙትን ኳስ በፍጥነት ከራሳቸው የግብ ክልል ለማውጣት ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም።


ከአጋማሹ ሩብ ደቂቃዎች በኋላ ባሉት ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ በመጠኑ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ነብሮቹ 16ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በየነ ባንጃ እና ሪችሞንድ ኦዶንጎ ሳጥን ውስጥ ተቀባብለው ያቀበሉትን ኳስ ያገኘው ሰመረ ሃፍታይ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በሴኮንዶች ልዩነትም አሜ መሐመድ በእነርሱ የግራ መስመር የፈጠረውን የግብ ዕድል ግብ ጠባቂያቸው ታፔ አልዛየር አቋርጦበታል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ጥራት ያላቸውን የግብ ዕድሎች በመፍጠሩ በኩል ውጤታማ ያልነበሩት ወልቂጤዎች የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን 32ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ በሀዲያ ተከላካዮች ሲመለስ ያገኘው ሳምሶን ጥላሁን ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶበት የግብ ዕድሉን አባክኖታል።


በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በየ ጥቂት ደቂቃዎች በሚወሰዱ የኳስ ቁጥጥር ብልጫዎች ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ቢደረጉም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ደካማ ነበር። ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ ሴኮንዶች ሲቀሩም የሀዲያ ሆሳዕናው ሠመረ ሃፍታይ ጉዳት ማስተናገዱን የተመለከተው የወልቂጤው የቀኝ መስመር ተከላካይ አብርሃም ኃይሌ ኳስ እየገፋ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚያደርገውን ሩጫ በማቋረጥ ወደኋላ ተመልሶ ለተጋጣሚው ቡድን ተጫዋች ያሳየው ስፖርታዊ ጨዋነት እጅግ የሚደነቅ እና የሚበረታታ ሆኖ ታይቷል።


ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ሀዲያዎች በኳስ ቁጥጥሩ ተሻሽለው በመቅረብ የተወሰደባቸውን ብልጫ ሲመልሱ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራም 52ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ግርማ በቀለ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ሠራተኞቹ በመልሶ ማጥቃት ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ራምኬል ሎክ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ከተጋጣሚ የሳጥን ጠርዝ ላይ የደረሰው አሜ መሐመድ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል።


ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ጋዲሳ መብራቴ ፣ መድን ተክሉ እና ስንታየሁ መንግሥቱን ቀይረው በማስገባት እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማነቃቃት ጥረት አድርገዋል። በዚሁ ጥረታቸውም 75ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ መብራቴ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ነው። ሆኖም በቀሪ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የጎላ የግብ ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።