መረጃዎች | 10ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጓል ፤ ሊጉ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከ ወልቂጤ ከተማ

የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

መቻል እና ንግድ ባንክን ገጥመው ሁለት ሽንፈቶች ያስተናገዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች አስፈላጊውን የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥብ ለማግኘት ወልቂጤን ይገጥማሉ። ቡድኑ ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ በአመዛኙ ዳዋ ሆቴሳን መዳረሻ ባደረጉ ረዣዥም ኳሶች እና የበየነ ባንጃ እንቅስቃሴ ባማከለ መልኩ ለማጥቃት ቢሞክርም ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት ይስተዋልበታል። በተለይም በንግድ ባንክ በተሸነፉበት ጨዋታ ይህንን ችግር ጎልቶ የታየበት ነበር። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በነገው ጨዋታ ለወትሮ ከሚታወቁበት ቀጥተኛ አጨዋወት ይወጣሉ ተብሎ ባይታሰብም ፍሬያማ ያልሆነው የማጥቃት ጥምረታቸው ላይ ግን ቢያንስ የተጫዋቾች ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሬ ይመስላል።

ሲዳማን በገጠሙበት ጨዋታ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸው ማሳካት የቻሉት ወልቂጤዎች ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎች አሳይተዋል። ኳስ ለመቆጣጠር የሚሞክር እና በሁለቱም መስመሮች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን ያስመለከተን አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የቡድኑ የፈጠራ አቅም ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ በነበረባቸው የጨዋታ ሂደቶች የፈጠራቸው ዕድሎች አናሳ መሆን የአጥቂ ክፍሉ ግብ እንዳያስቆጥር አድርጎታል። አሰልጣኙ አሁንም በዋነኝነት በአሜ መሐመድ የሚመራውን የቡድኑ የመስመር አጨዋወት ዋነኛ የማጥቂያ መሳርያው አድርጎ ይጠቀማል ተብሎ ይገመታል።

በወልቂጤዎች በኩል አቡበከር ሳኒ፣ መሳይ ጳውሎስ እና በቃሉ ገነነ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። የሀዲያ ሆሳዕናዎቹ ኋላሸት ሰለሞን እና ሔኖክ አርፊጮ ከጉዳት ተመልሰዋል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ ተገናኝተው አምስቱ ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲጠናቀቁ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ የተቀረችውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ችለዋል። በጨዋታዎቹ ነብሮቹ ስድስት ሠራተኞቹ ደግሞ ሦስት ግቦች ሲኖራቸው የአምናዎቹ ሁለት ግንኙነቶቻቸው ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ።

ጨዋታው በዮናስ ካሳሁን የመሐል ዳኝነት ይመራል፤ አማን  ሞላ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን የሚመራው ኤልያስ  መኮንን ደግሞ ረዳት ዳኞች ሆነው ተመድበዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው አራተኛ ዳኛ በመሆን ጨዋታውን ይመሩታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሻሸመኔ ከተማ

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሻሸመኔ ከተማዎችን የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

በሁለት ጨዋታ ስድስት ነጥቦች አስመዝግበው ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመቀጠል ሻሸመኔን ይገጥማሉ። ፈረሰኞቹ ባደረጓቸው ጨዋታዎች የሊጉን ከፍተኛው የግብ መጠን ማስቆጠር የቻሉ ሲሆን አቤል ያለው፣ አማኑኤል ኤርቦና ተገኑ ተሾመ የሚመሩት የአጥቂ ክፍላቸውም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። ሦስቱ የቡድኑ የማጥቃት ክፍል የሚመሩት ተጫዋቾች በድምሩ አምስት ግቦች ማስቆጠርም ችለዋል።

ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን በሚሰጡ ሁለት አማካዮች የተገነባ መሃል ክፍል ያላቸው አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በነገው ዕለትም መስመሮችን አብዝቶ የሚጠቀም የማጥቃት አጨዋወት ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአዲሱ የውድድር ዓመት ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት አዲስ አዳጊዎቹ ሻሸመኔ ከተማዎች የመጀመርያው የሊግ ነጥባቸው ለማሳካት ከፈረሰኞቹ ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል። ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ኳስን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርግም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ትልቅ ክፍተት ይስተዋልበታል፤ በ180 ደቂቃዎች ግብ አለማስቆጠራቸውም የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግር ማሳያ ነው።

ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል ያላቸው ሻሸመኔዎች የነገው ተጋጣሚያቸው በአማካይ በጨዋታ ሦስት ግቦች እያስቆጠረ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ቡድን እንደመሆኑ በመከላከሉ ረገድ ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቃቸው እሙን ነው።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጉዳት ላይ ያለው ቢንያም በላይ ለጨዋታው ዝግጁ አይደለም፤ በቅርቡ ወደ ልምምድ የተመለሱት ባህሩ ነጋሽ እና አማኑኤል ተርፋም ከጉዳታቸው ቢያገግሙም ለጨዋታው የመድረሳቸው ዕድል ጠባብ ነው። በአማኑኤል ምትክ ወደ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ብሩክ ታረቀኝም በቋሚነት ጨዋታውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ተከትሎም ፈረሰኞቹ አሸናፊው ቡድን ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሻሸመኔዎች በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ክለቦቹ በሊጉ ሁለት ጊዜ ተገናኝተው በነበሩበት በሚድሮክ ስም በተሰየመው የሁለት ሺው ውድድር በሁለቱም አጋጣሚዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

የምሽቱን ጨዋታ ተከተል ተሾመ በዋና ዳኝነት ይመሩታል፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና አዲሱ የሊጉ ዳኛ ሰለሞን ተስፋዬ በረዳትነት፤ በሪሶ ባላንጎ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል።