ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ጣፋጭ ድል ተጎናጽፏል

 ፈረሠኞቹ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው ሻሸመኔ ከተማን 3ለ2 ረተዋል።

በምሽቱ መርሐግብር በሊጉ አናት እና ግርጌ ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሻሸመኔ ከተማ ሲገናኙ ፈረሠኞቹ የባለፈው ድላቸው ላይ የተጠቀሙበት አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ከሀዋሳ ሽንፈታቸው አንፃር ሻሸመኔዎች ጉዳት ባስተናገደው ቻላቸው መንበሩ ምትክ ያሬድ ዳዊትን ተክተው ገብተዋል።


12፡00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ ለተመልካች ማራኪ የሆነ ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሻሸመኔዎች ኳስ በሚያጡ ሰዓት በአምስት ተከላካይ አደራደር በመቆም በሚያገኙት ኳስ በፈጣን ሽግግር የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ፈረሠኞቹ በአንጻሩ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው በመግባት ተጭነው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም 5ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ዳዊት ተፈራ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ በግሩም ሁኔታ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከራሳቸው የግብ ክልል ሲወጡ በቁጥር ቢበለጡም በተጫዋቾቻቸው ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ታግዘው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ሻሸመኔዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ያሬድ ዳዊት በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ጊዮርጊሶች 18ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ናትናኤል ዘለቀ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

የሻሸመኔ ተጫዋቾች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወታቸው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ እንዲደርሱ ምክንያት የሆነላቸው ፈረሠኞች 33ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ግብ አስቆጥረዋል። ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የቅጣት ምት አቤል ያለው በአስደናቂ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ባለፉት ጨዋታዎች ውጤት ከማጣቸው አንጻር የያዙትን ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት በጥንቃቄ መጫወት የመረጡት ሻሸመኔዎች ከመስመር ተከላካዮቻቸው በሚነሱ ኳሶች ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት ሲሞክሩ የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። ሆኖም 45ኛው ደቂቃ ላይ ግን ተጨማሪ ግብ ሊቆጠርባቸው ነበር። ዳዊት ተፈራ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል ፈረሠኞቹ በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃ በዳዊት ተፈራ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ለግብ ለቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይም ሄኖክ አዱኛ በግራ መስመር የተሻማው የማዕዘን ምት በተከላካዮች ሲመለስ አግኝቶት ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ሲይዝበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ተገኑ ተሾመ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የተሻለ የግብ ዕድል ቢያገኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።

ሻሸመኔዎች ቀስ በቀስ ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው በመውጣት ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ 57ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የግብ አጋጣሚያቸውን በአለን ካይዋ አማካኝነት ቢያገኙም በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ የገባው አጥቂው እጅግ በዘገየ ውሳኔ ሳይጠቀምበት ሲቀር በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ያሬድ ዳዊት በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ራሱ አጥቂው አለን ካይዋ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎት ሻሸመኔን በድጋሚ ወደ መሪነት መልሷል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተቀዛቅዘው ከነበሩበት የጨዋታ ሂደት ተጋግለው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 78ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በቀኝ መስመር ከሳጥን አጠገብ የተገኘውን የቅጣት ምት ረመዳን የሱፍ ለበረከት ወልዴ ሲያቀብል ኳሱን ያገኘው ተቀይሮ የገባው አማካዩ በረከት በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ባላቸው የማጥቃት ኃይል ሁሉ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ሲታትሩ የነበሩት ፈረሠኞች 97ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው አሸናፊ የሚሆኑበትን ወርቃማ አጋጣሚ አግኝተዋል። ተቀይሮ የገባው ሞሰስ ኦዶ በግራው የሳጥኑ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ አምበሉ ወጋየሁ ቡርቃ ጥፋት በመሥራቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አቤል ያለው ወደ ግብነት ቀይሮታል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።