የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 ሻሸመኔ ከተማ

“ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር ፣ ዘጠና ደቂቃ ትልቅ ፉክክር የተደረገበት ነው” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

“በጨዋታው የተሻልን ነበርን ፣ በጥቃቅን ስህተቶች ውጤቱን ልናጣ ችለናል” አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ

በግቦች የታጀበው የምሽቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሻሸመኔ ከተማ ጨዋታ በፈረሰኞቹ የ3ለ2 ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቆይታን አድርጋለች።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ – ሻሸመኔ ከተማ

ሁለት ጊዜ መርተው ስለመሸነፋቸው…

“በጣም አሳዛኝ ነው። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥለን ነበር ፣ የዛሬን ጨዋታ ለማሸነፍ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው ፣ በጨዋታው የተሻልን ነበርን በጥቃቅን ስህተቶች ውጤቱን ልናጣ ችለናል።”


ሁሉም ግቦች ከቆሙ ኳሶች ስለ መቆጠራቸው ..

“አንዳንድ ጊዜ ድካም ሲኖር የኮንሰንትሬሽን ችግር ይኖራል ፣ በዛ ሒደት ውስጥ እንደነዚህ ያሉ ዕድሎችን መጠቀም ያስፈልጋል ፣ እኛም ተጠቅመን ነበር ፣ ሁላችንም በሰራነው ልክ የጎል ዕድሎችን አግኝተናል ፣ ውጤቱ በጣም አሳዛኝ ቢሆንም ተጫዋቾቼ ደክመዋል ለፍተዋል ነጥብ ማግኘት ነበረብን አልተሳካም።”

የዛሬው ውጤት በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ …

“ምንም የሚኖረው ነገር የለም ፣ ሁልጊዜ ለእያንዳንዱ ጨዋታ ዝግጅ ነን ፣ ለምን ለሚቀጥለው ጨዋታ መዘጋጀት አለብን ውድድሩ ገና ነው ፣ አልተጀመረም ገና ስለዚህ እኛ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ያለፈው ዓመት ልምድ ያላቸውን ክለቦች ነው በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ያገኘነው ፣ ያለፉትም ጨዋታዎች በቀላሉ በስህተት ነው ጎሎች የተቆጠሩብን አሁንም እነዚህን ጥቃቅን ስህተቶች አስተካክለን ወደ አሸናፊነት የማንመለስበት ምንም ምክንያት የለም።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር ዘጠና ደቂቃ ትልቅ ፉክክር የተደረገበት ነው ፣ ያገባሉ እናገባለን ፣ ያገባሉ እናገባለን መጨረሻ ላይ ግን ተጫዋቾቼ ጥሩ ነገር አድርገው ሦስት ነጥብን ይዘን ወጥተናል።”

ከመመራት ተነስቶ ማሸነፍ ስለ መቻላቸው እና ስለ ጨዋታው ክብደት…

“ሻሸመኔ ትንሽ ነው የሚባል ቡድን አይደለም። ሁሉም ቡድን ጠንካራ ነው ፣ ከእኛ ጋር ሲቀርቡ ደግሞ ሁለት መቶ ፐርሰንት ጠንካራ ሆነው ነው የሚቀርቡት ፣ ሻሸመኔ በጣም ጥሩ ቡድን ነው ፣ በሽግግር ነበር እኛ ላይ ለማግባት የሚሄዱት ፣ ያንን ተቋቁመን አግብተው አግብተን ተጫዋቾቼ ያላቸውን ኳሊቲ ተጠቅመው ማድረግ ያለብንን አድርገን የተሻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲያሸንፍ አድርገናል።”

ስለአቤል ያለው ተደጋጋሚ ግቦችን ማስቆጠር…

“አቤልን ከዚህም በላይ ነው የምጠብቀው። ገና አቤል አላገባም ብዬ ነው የማስበው ፣ ብዙ ጎሎችን ማግባት ይችላል። ለክለቡ ትልቅ ማማ መሆን ይችላል ፣ ለምን ተጫዋቾቼ የሚያደርጉትን ተጋድሎ እያየህ ነው። ለቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ነገር እየሰሩ ነው ፣ የተሻለ ነገር የሚሰሩ ተጫዋቾችም አሉ እኛም ያየነው ያንን ነው።”