የአሰልጣኞች አስተያየት | ሻሸመኔ ከተማ 1-3 ሲዳማ ቡና

“ያሰብነው ነገር ተሳክቶልናል ፣ አሁን ተጫዋቾቼም የዚህ የማሸነፍ ሥነ ልቦናቸውም እያደገ ይመጣል” አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

“የዳኞች ውሳኔ ላይ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እያየሁ ነው” አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ

የአራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ተከናውኖ ሲዳማ ቡና ሻሸመኔ ከተማን 3ለ1 በመርታት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን ካሳካበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ – ሻሸመኔ ከተማ

ቡድኑ በእንቅስቃሴ ጥሩ እየሆነ ዛሬን ጨምሮ በተደጋጋሚ ውጤት ስለ ማጣቱ ..

“ስንመጣ ለማሸነፍ ነበር ፍላጎታችን ፣ ያለፈውን ውጤት ቁጭት ለመለወጥ ነበር የመጣነው ፔናሊቲውን እስኪያገኙ ድረስ ቡድኑ ጥሩ ነበር። ከዛ በኋላ ባሉ እንቅስቃሴዎች ምንም በማይታወቅ መልኩ የተጫዋቾቼ መቀዛቀዝ ታይቷል ዛሬ ያ መቀዛቀዝ እኔ ቡድን ላይም እስከዛሬ የሚታይ አይደለም። በተነሳሽነትም በኳስም በተለያዩ የኳስ ሂደቶች ፣ አማራጮችን መጠቀም ላይ ተጫዋቾቼም በደንብ እየሰራውባቸው ነው ግን ውጤት አስጠብቆ ተቆጣጥሮ መውጣት ላይ ዛሬ ደግሞ ከባለፈው የበለጠ የወረደ እንቅስቃሴ ነው ያደረግነው። ተጫዋቾችን የበለጠ ማነሳሳት ነው የምንፈልገው ውድድሩ አላለቀም ገና ነው ስራችን ነው ፣ እኔም ስራዬ ነው ተጫዋቾቹም ፕሮፌሽናል ናቸው ስራቸው ነው ፣ የሚቆም ነገር የለም አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገሮች ያጋጥማሉ። ስለዚህ መቋቋም ነው ምንም ማድረግ አይቻልም ፣ ለሚቀጥለው ነገር ማሰብ ነው። ከዚህ በኋላ ሌላ የምናስበው ነገር የለም ትንሽ ቅር ያለኝ ምንድነው በጣም ዛሬ መቀዛቀዝ ታይቷል። በእንደዚህን ያህል የእኔ ቡድን ብልጫ ተወስዶበት ተሸንፎም አያውቅም ፣ ወደፊት መርምረን እንቅስቃሴውን አስተካክለን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋለን ፣ እግር ኳስ ነው ምንም ማድረግ አይቻልም አንዱ የእግር ኳስ ባህሪ ነው።”

አጨቃጫቂ ስለነበረችው የፍፁም ቅጣት ምት…

“አያሰጥም። ዳኛው አጠገቡ ቅርብ እያለ ነው የመስመር ዳኛው ነው በግፊት ሄዶ እንዲሰጥ ያደረገው ፣ አንደኛ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ ነው የተፈፀመው ፣ ሁለተኛ ሀምሳ ሀምሳ ነው የተገናኙት ፣ የዳኞች ውሳኔ ላይ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እያየሁ ነው። ፌድሬሽኑ ሊያርመው ወይም ማስተካከያ ያድርግባቸው እንጂ የዚህ ፔናሊቲ መግባት ቡድናችን ላይ ጫና የፈጠረ ይመስለኛል ጎሉ እስኪገባ የተሻልን ነበርን።

በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በመጨረሻ ደቂቃ ስለሚቆጠርባቸው ጎሎች…

“አንደኛ የእኔ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው ፣ ያለፈውን ጫና ፣ ያለፈውን ሽንፈት ውስጣቸው አቆይተው ነው የሚጫወቱት እና ያንን ለመካስ በሚያደርጉት ጥረት የመጨረሻ ሰዓት ላይ ደግሞ የኮንሰንትሬሽን ማጣቶች ይኖራሉ። ወደ ኋላ ማፈግፈጎችም ይታዩ ነበር። በዛ ምክንያት ድንገተኛ ጎሎች ገብተውብናል ፣ የዛሬው አልተሳካም ውጤት ይዘን ለመውጣት ነበር አስበን የመጣነው ምንም ማድረግ አንችልም ስለሚቀጥለው ነው ማሰብ ያለብን።”

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ስለ ሁለቱ የጨዋታ አጋማሾች…

“ጨዋታችን ጥሩ ነው ፣ በተለይ ከፋሲል ጀምሮ ያለ ለውጥ አለ ፣ ከፋሲል ጋር አቻ ልንወጣ የምንችልበት ነበር አልተሳካም። ዛሬ ለሁላችንም የምንጠብቀው ማድረግ የሚገባንን እንደ ግዴታ ነበር ዛሬ ሦስት ነጥብ ማግኘት ፣ ካልሆነ ጫናው እየበዛ ይሄዳል ፣ በተጫዋቾቼም በሁላችንም ላይ እንደገና ቀጣይ ጨዋታ ከሀዋሳ ጋር የደርቢ ጨዋታ ነው ፣ ስለዚህ ይሄን ነጥብ ለመያዝ ሳምንቱን ሙሉ በክፍልም ፣ በሜዳም እንዲሁም በግልም በቡድንም ብዙ ነገር ሞክረናል ፣ ያሰብነው ነገር ተሳክቶልናል አሁን ተጫዋቾቼም የዚህ የማሸነፍ ስነ ልቦናቸውም እያደገ ይመጣል እና የተሻለ ቡድን እየሆነ ይመጣል ብዬ አስባለሁ።”

ፊት ላይ ካሉ አጥቂዎች ጎሎችን እያገኙ ስላለመሆናቸው …

“አሁን ለምሳሌ ማይክል አዲስ የመጣ ተጫዋች ነው ፣ አንዴ መስመሩን እስከሚያገኝ ነው ፣ የሚሻሻል ልጅ ነው ምንም ማድረግ አይቻልም ፣ ይገዙም ሆነ አጃህ በሽታ ላይ ናቸው ፣ ስለዚህ ባሉህ ተጫዋቾች መጠቀም ያስፈልጋል እና ይሄ ነገር ግን እያደገ ይሄዳል። ስፔሻሊ አጃህ ቶሎ ይመለሳል ብዬ አስባለሁ።”

ከአማካይ ተጫዋቾች በቂ የግብ ዕድል አለመፈጠሩ…

“አማካይ ላይ አሁን ማሳደግ ያለብን ምን መሰለህ ፣ ከዚህ በፊት ስንቸገር የነበረው መሐል ሜዳ ላይ በተቃራኒው እንበለጣለን ፣ ያንን አሁን ባላንስ ወደ ማድረግ መጥተናል ፣ ከዚህ በኋላ ደግሞ ማሳደግ የሚገባው ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ አማካዮቹ ራሳቸው አግቢ መሆን አለባቸው ፣ ጥሩ ሰጪ መሆን አለባቸው። ይሄ በሂደት ኦያደገ ስለሚመጣ ይሄ ይሻሻላል ብዬ አምናለሁ።”

ይገዙ ፣ አጃህ እንዲሁም የአብዱራህማን (ግሪዳው) ጉዳቶች…

“ይሄን መገመት ይከብዳል። ለምሳሌ ይገዙ ዛሬ ይጫወታል ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ልምምድ ላይ ገብቶ ሲሳተፍ እንደገና የተነሳበት በዚህ ምን ያህል ይቆያል ዕርግጠኛ አይደለሁም። አጃህ ይመለሳል ብዬ አስባለሁ ፣ የአብዱራህማንም ራሱ መጥፎ አጋጣሚ ነው ያጋጠመን ባሉን ተጫዋቾች ግን እየሰራን እንሄዳለን ብዬ አስባለሁ።”

በአራቱ ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ስለ ማስተናገዳቸው…

“አይተሀቸው ከሆነ የሚቆጠሩ ጎሎች ባለቀ ሰዓት አካባቢ በቆሙ ኳሶች ፣ የኮንሰንትሬሽን ችግር ፣ የመናበብ ችግር ፣ የመዘናጋት ችግር እነዚህ ነገሮች ናቸው እና ዛሬ ደግሞ ይሄ በመጠኑ ተቀርፏል። ይሄን እያሻሻልን መሄድ አለብን።”