ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል

በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ሲዳማ ቡና ሻሸመኔ ከተማን 3-1 በመርታት የመጀመሪያ ሦስት ነጥቡን አግኝቷል።

በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ሻሸመኔ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ሲገናኙ ሻሸመኔዎች ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት አንፃር ወጋየሁ ቡርቃን አሳርፈው በኤቢሳ ከድር የቀየሩበት ብቸኛው ለውጣቸው ሲሆን በፋሲል ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማዎች በበኩላቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መክብብ ደገፉ ፣ ጊት ጋትኩት እና ደግፌ አለሙ አርፈው መሐመድ ሙንታሪ ፣ ብርሀኑ በቀለ እና አንተነህ ተስፋዬ ተክተዋቸዋል።


ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ በመውሰድ በአብዛኛው በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ሻሸመኔዎች በበኩላቸው በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት የሲዳማ የተከላካይ መስመር ኳስ እንዳይጀምር በመከልከል በሚያገኙት ኳስ ወደ ሳጥን ለመድረስ ጥረት አድርገዋል።

መጠነኛ ብልጫ የወሰዱት ሲዳማዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ 8ኛው ደቂቃ ላይ በማይክል ኪፖሩል አማካኝነት አድርገው በግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ተመልሶባቸዋል። በስድስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ በሻሸመኔ በኩል አጥቂያቸው አለን ካይዋ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው 26ኛው ደቂቃ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ከሳጥን ጫፍ ማይክል ኪፖሩል ላይ ጥፋት በመሥራቱ በአጨቃጫቂ ሁኔታ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ደስታ ዮሐንስ አስቆጥሮት ሲዳማ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል። ሆኖም ግን ሻሸመኔዎች በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በአሸብር ውሮ አማካኝነት በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ተጨማሪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

ያን ያህል የጋለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳያስመለክተን በየ ጥቂት ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በሁለቱም በኩል እየተወሰደበት በቀጠለው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ሲዳማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሀብታሙ ገዛኸኝ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ወደ ሳጥኑ የቀኝ ክፍል የደረሰው ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን አንድ ተጫዋች አታልሎ በማለፍ በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ቀዝቃዛነት በዛው ሲቀጥል የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አይሁን እንጂ በማጥቃት እንቅስቃሴ ብልጫውን የወሰዱት ሲዳማዎች የአጋማሹን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራም 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ኳሱን በጥሩ ክህሎት ገፍቶ መውሰድ የቻለው ማይክል ኪፖሩል ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ይዞበታል። ይህ አጥቂ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ከቀኙ የሳጥን ጠርዝ ላይ ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል።

እንደሚያደርጉት ስኬታማ ቅብብል ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን መድረስ ያልቻሉት ሻሸመኔዎች ቀስ በቀስ ወደ ተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሲመጡ እዚሁ መነቃቃታቸው ላይ ግን 68ኛው ደቂቃ ላይ ውሃ ሊቸለስባቸው ነበር። ደስታ ዮሐንስ በጥሩ ዕይታ ሰንጥቆ ባቀበለው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው ማይክል ኪፖሩል በደካማ እና የዘገየ ውሳኔ ወደ ግብ ሳይሞክረው ግብ ጠባቂው ደርሶ መልሶበት የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

ዝናባማ የዓየር ሁኔታ በነበረባቸው የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ፉክክሩ እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል ሻሸመኔዎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳዩም የሲዳማን የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው ለመግባት ተቸግረዋል። ሆኖም 83ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማዎች በደስታ ዮሐንስ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ኤቢሳ ከድር በግሩም ቦታ አያያዝ ተደርቦ ሲያመክንባቸው በሴኮንዶች ልዩነት ግን ተቀይሮ የገባው ደግፌ ዓለሙ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ በጥሩ አጨራረስ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ያለፉትን 85 ደቂቃዎች በሚያስረሱት የመጨረሻ ድንቅ 5 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል በብርቱ ፉክክር ግብ ተቆጥሮበታል። በቅድሚያም አበባየሁ ዮሐንስ በተከላካዮች ተጨርፋ መረቡ ላይ ያረፈች ግብ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሲያስቆጥር በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ በሻሸመኔ ከተማ በኩል ተቀይሮ የገባው ኢዮብ ገብረማርያም በተመሳሳይ በተከላካይ ተጨርፋ የገባች ግብ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ማስቆጠር ችሎ ቡድኑን ለዜሮ ከመሸነፍ አድኗል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።