መረጃዎች| 13ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

ሻሸመኔ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ሦስተኛው ሳምንት ላይ በደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስት ሽንፈቶች አስተናግደው ምንም ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት ሻሸመኔ ከተማዎች የሊጉን የመጀመርያ ነጥብ ለማስመዝገብ ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ሽንፈት ባስተናገዱበት የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ግባቸውን ማስቆጠር የቻሉት አዲስ አዳጊዎቹ በሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች አስተናግደዋል። ሻሸመኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥሩ የመሻሻል ሂደት ላይ ያለ ቡድን ነው ፤ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ ያሳዩት መልካም እንቅስቃሴም ለዚ ማሳያ ነው። በጨዋታው በሚያጠቁ ጊዜ 3-5-2 የሚመስል አቀራረብ ይዘው በሁለቱም የክንፍ ተጫዋቾች አሸብር ውሮ እና ያሬድ ዳዊት ለማጥቃት የሞከሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ነገም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል። ከተጠቀሱት ተጫዋቾች ወደ ሳጥን የሚላኩ የተሳኩ ረዣዥም ኳሶችም የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳርያ ሆነው ይቀጥላሉ ተብሎ ይገመታል። ሆኖም በቆመ ኳስ መከላከል ላይ ያላቸውን ድክመት ግን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።

እንደ ባለፈው የውድድር ዓመት ዘንድሮም መጥፎ አጀማመር ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች ልክ እንደ ተጋጣሚያቸው ጥሩ አጀማመር አላደረጉም። ከሦስት ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ነጥብም አንድ ብቻ ነው። በነገው ጨዋታም የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ድል ለማግኘት አልመው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ ፋሲልን በገጠመበት ጨዋታ ምንም እንኳ ሽንፈት ቢያስተናግድም በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ መሻሻሎች አሳይቷል። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በተነሳሽነት ረገድ ያሳዩት ለውጥም በትልቁ ይነሳል። ሆኖም የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ድክመታቸው አሁንም ግቦችን እንዳያስቆጥሩ እክል ሆኖባቸዋል። በወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት ጠባብ የአጥቂ አማራጭ ያላቸው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በመጨረሻው ሳምንት ጥሩ የተንቀሳቀሰው ስብስባቸውን ያስቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በጥራትና በቁጥር ላቅ ያሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር ትልቁ የቤት ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

በሻሸመኔ በኩል በሁለተኛው ሳምንት ተጎድቶ ከሜዳ የወጣው ቻላቸው መንበሩ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። በሲዳማ ቡና በኩል ይገዙ ቦጋለ እና ጋናዊው አጥቂ ፊሊፕ አጃህ በጉዳት አሁንም ቡድኑን አያገለግሉም። ሙሉቀን አዲሱ ከቅጣት ሲመለስ መሐመድ ሙንታሪ የወረቀት ሥራዎቹ አልቀው በቋሚ አሰላለፍ ነገ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በነገው ዕለት የሚገናኙ ይሆናል።

ፌዴራል ዳኛ ዓባይነህ ሙላት በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤልና እሱባለው መብራቱ ደግሞ በረዳት ዳኝነት ፣ ዮናስ ካሳሁን በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ጨዋታውን ይመሩታል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በአንድ ነጥብ ልዩነት በተቀራራቢ ደረጀ ላይ የሚገኙት ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ሰብስበው በ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ድል ፣ አቻ እና ሽንፈት ቀምሰዋል። የተቆጠረባቸው ግብና ያስቆጠሩት የግብ ብዛትም ተመሳሳይ ነው። በሦስቱም ጨዋታዎች የተለያየ ቋሚ አሰላለፍ የተጠቀሙት ብርቱካናማዎች በአጨዋወት ላይም በተመሳሳይ ወጥነት ይጎድላቸዋል፤ ቡድኑ በሦስቱም ጨዋታዎች ኳስ በመቆጣጠር በመስመሮች ለማጥቃት የሚሞክር እና በረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ሆኖም በአጨዋዎቶቹ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገር ተስተውሏል ፤ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ምንም ግብ አለማስቆጠራቸውም የዚ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ አስራት አባተ በነገው ጨዋታ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለውን ባንክ እንደ መግጠማቸው የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት መጨመር ግድ ይላቸዋል።

ከሦስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦች ሰብስበው በ7ኛ ደረጃነት የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ወደ ሊጉ አናት ለመጠጋት የሚያስችላቸውን ነጥብ ፍለጋ ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማሉ። ንግድ ባንኮች እስካሁን ባካሄዷቸው ጨዋታዎች ሁለት ግቦች አስቆጥረው አንድ ግብ የተቆጠረባቸው ሲሆን በሁለት ጨዋታዎችም ግባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል ፤ ከዚ በተጨማሪ በክፍት የጨዋታ ሂደት ግብ ያላስተናገደው ጠንካራው የመከላከል አደረጃጀታቸው የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው።

መቻልን በገጠሙበት ጨዋታ ከሌላው ጊዜ በተለየ ተሻሽለው የቀረቡት ንግድ ባንኮች በተለይም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል የነበራቸውን ክፍተቶች በመጠኑ ቀርፈዋል ፤ በመጨረሻው ጨዋታ ምንም እንኳ አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር ቢችሉም በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ኪቲካ ጅማ ፣ አዲስ ግደይና ባሲሩ ዑመርም የማጥቃት አጨዋወቱ ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው።

በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል ያሲን ጀማል፣ ተመስገን ደረሰና አብዱልፈታህ አሊ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። በንግድ ባንክ በኩል ግን በቅጣትም ሆነ በጉዳት ጨዋታው የሚያመልጠው ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ አምስቱን ማሽነፍ ቀዳሚ ሲሆን ባንክ አራቱን በድል አጠናቋል። ሦስቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 21 ጎሎች በተቆጠሩበት የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ አንድ ጊዜ ብቻ ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲሆን ባንክ 11፣ ድሬ 10 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ባህሩ ተካ በመሐል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና አስቻለው ወርቁ በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ተደርገው ተመድበዋል።