የትግራይ ክለቦች ቀጣይ ሁኔታ ላይ ውሳኔ ተላለፈ

የትግራይ ክለቦች በዘንድሮ የውድድር ዓመት የሚሳተፉበት ሊግ ታውቋል።

ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከነበሩበት ሊግ አንድ ደረጃ ወርደው እንዲሳተፉ የተወሰነላቸው የትግራይ ክለቦች በዘንድሮ የውድድር ዓመት በክልል አቀፍ ውድድር ብቻ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል። ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ስላልተሰጠን ብለው ከቀናት በፊት በተካሄደው የከፍተኛ ሊግ የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ያልተሳተፉት መቐለ 70 እንደርታ ፣ ስሑል ሽረና ወልዋሎን ጨምሮ ስምንት ክለቦች እና የትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን ዛሬ ከሰዓት ባደረጉት የጋራ ስብሰባ ይህንን ውሳኔ መወሰናቸው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ውድመት የደረሰባቸው ክለቦቹ ያለባቸው የፋይናንስ ችግር እና የዝግጅት እጥረት ምክንያት ለዚህ ውሳኔ ለመድረስ እንዳበቃቸውም ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።


ዛሬ በተካሄደው ስብሰባም በውድድሩ ደንብ ፣ የደሞዝ ጣርያ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መግባባት የተደረሰ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያት ተሳታፊ ክለቦች ከፌደሬሽኑ ጋር በሚያደርጉት ተመሳሳይ ውይይት ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የውድድር ዓመት ክለቦቹ ወደ ሀገራዊ ውድድሮች ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ሰምተናል።

በተያያዘ ዜና ክለቦቹ የክልሉ ክለቦችን ለመደገፍ አልሞ የሚዘጋጀውን የገቢ ማሰባሰብያ መርሐ-ግብር አፈጻጸም ገምግመዋል። በዚህ መሰረትም ከዚህ ቀደም በሁለት ድርጅቶች ታስቦ የነበረውን መርሐ-ግብር Ey Production ብቻውን እንዲያዘጋጀው ክለቦቹ ወስነዋል።