የሉሲዎቹ አለቃ ከወሳኙ ጨዋታ አስቀድሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

👉 “እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ጥሩ ውጤት ይዘን እንደምንወጣ ነው”

👉  “እኔ ሁልጊዜ በተጫዋቾቼ ላይ ትልቅ እምነት አለኝ”

👉  “የዝግጅት ጊዜው ቢያንስም የተሻሉ ነገሮች እንሠራለን ብዬ አምናለሁ”

በፈረንሳይ ፓሪስ ለሚካሄደው ኦሎምፒክ በአፍሪካ ዞን የሚወክሉ ሁለት ሀገራትን ለመምረጥ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች ተጠናቀው ከነገ ጀምሮ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያዎች የሚጀምሩ ይሆናል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ጋር ካለባት የሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ አስቀድማ ቻድን በሰፊ የጎል ልዩነት በመርታት ለሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ማለፏ ይታወቃል። ነገ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያደርጉት ሉሲዎቹ በዋና አሰልጣኛቸው ፍሬው ኃይለገብርኤል አማካኝነት ከጨዋታው አስቀድሞ ዝግጅታቸውን አስመልክቶ ዛሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሰልጣኙ በመግቢያ ንግግራቸው ለሰባት ቀን ዝግጅታቸውን ሲሠሩ መቆየታቸውን እና ቡድኑን በዋናነት ከ20 እና 18 ዓመት በታች ቡድን ማዋቀራቸውን በመግለጽ ለነገ ጨዋታ የሚሆነውን ልምምድ በተጨማሪ በስነ ልቦና በኩል በጥሩ ሁኔታ ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተው ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።


የዝግጅት ጊዜ ማነሱ ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ…?

የዝግጅት ጊዜው አጭር ስለሆነ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ብዙ ተጫዋቾች ለማካተት የተፈለገው ብዙ ልምምድ የሠሩ ተጫዋቾችን ማሰባሰቡ አስፈላጊነቱ ሰፊ በመሆኑ ነው። ሁለተኛ ቡድኑ የተዋቀረው ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ካነሳው ስብስብ ሲሆን እኔ ትኩረት የማደርገው ለረጅም ዓመት ለብሔራዊ ቡድኑ ግልጋሎት የሚሰጡ ተጫዋቾች ከማሰብ አኳያ ስለሆነ አሁን የአፍሪካ ዋንጫ ፣ የዓለም ዋንጫ መግባት እንደ ውጤት የሚያስፈልግ ቢሆንም ግን ለረጅም ዓመት መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን የማምጣት ደግሞ ግዴታ አለብኝ ብዬ አስባለው። ስለዚህ የዝግጅት ጊዜው ሰባት ቀን መሆኑ ከዕረፍት ለመጡት የሚከብድ ቢሆንም አብዛኞቹ ከ20 ዓመት በታች የተጫወቱ ተጫዋቾች በመሆናቸው እና የቀጠለ ቡድን ስለሆነ የዝግጅት ጊዜው ቢያንስም የተሻሉ ነገሮች እንሠራለን ብዬ አምናለሁ።

ስለ ናይጄሪያ ጥንካሬ…?

የናይጄሪያ ቡድን ውስጥ ከባርሴሎና ፣ ከፒኤስጂ እና ከሌሎች ክለቦች የመጡ ተጫዋቾች እንዳሉ እናውቃለን። የእኛ ተጫዋቾች አሁን እየተሠራባቸው ያለው ምንድን ነው ፤ እግርኳስ ወቅታዊ አቋም ነው ፤ ስም ወይም ሀገር ተሸክሞ በአፍሪካ ፣ በዓለም እና በኦሎምፒክ ውድድር ናይጄርያዎች ያላቸው ስም ይቀመጥ እና የእኛ ተጫዋቾች ላይ ከሜዳ ውጭ በንድፈ ሀሳብ ብዙ ሥራዎችን ሰርተናል። አንድ ለአንድ ነው የሚገቡት ፣ እነርሱም ሁለት እግር ፣ ሁለት እጅ ፣ ሁለት ዓይን ይዘው ነው የሚገቡት የእኛም እንደዛው ልዩነቱ ግን የተዘረጋው ሲስተም ወደ ተሻለ መንገድ የመሄዱ እና ያለመሄዱ ጉዳይ ነው። በዚህ ዙሪያ ከተጫዋቾቼ ጋር ሰፊ ውይይት አድርገናል። አንድ ቡድን የተጫዋች ጥራት ስለያዘ ብቻ ያሸንፋል የሚለው ነገር ላይ ወደ ድምዳሜ ባንመጣ። የእኛ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ እግርኳስ የሚፈልገውን ትክክለኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ ምንም ነገር ለማድረግ የተሻለ ሥራ እንደሚሠሩ አስረድተናቸዋል። የዕድል ጉዳይ እንጂ የኛም ተጫዋቾች የተሻለ ደረጃ የሚደርሱበት አጋጣሚ እንዳለ መናገር እፈልጋለሁ።

ከጨዋታው ምን እንጠብቅ…?

በእግርኳስ ማንኛውም አሰልጣኝ በሠራው ልክ በራስ መተማመን ነው ለጨዋታው የሚቀርበው ፤ እኔ ደግሞ ሁልጊዜ በተጫዋቾቼ ላይ ትልቅ እምነት አለኝ። መሠራት ያለበት ሥራ ከተሠራ ምንም ነገር ማድረግ የሚችሉ ተጫዋቾች ስላሉኝ በጣም በራስ መተማመን ለማሸነፍ ነው የምንገባው እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ጥሩ ውጤት ይዘን እንደምንወጣ ነው።

ጨዋታው በሚደረግበት ሜዳ ልምምድ ስላልሠሩበት ምክንያት…?

አበበ ቢቂላ ስታዲየም ፍቃድ ሰጥተውን በፈለግንበት ሰዓት በጥሩ ሁኔታ እየሠራን ነው። ሆኖም ግን ሜዳው ከእኛ ተጫዋቾች አቅም ጋር ተመጣጣኝ ሆኖ በሙሉ አቅም ለመሥራት ሜዳው ትንሽ የተቸገርንበት ነገር አለ። ያንን ለመቀነስ በሌሎች ሜዳዎች የተሻሉ ነገሮችን ለመሥራት እና አጠቃቀማችንን እኛ በምንፈልገው መንገድ ለማድረግ በተለያዩ ሜዳዎች ለመሥራት መርጠናል።

ከአማካይዋ ንቦኝ የን እና ከሌሎች ተጫዋቾች ጉዳት ጋር ተያይዞ ያሉ ነገሮችን በተመለከተ…?

ከጉዳት ጋር ተያይዞ እስካሁን ባለኝ መረጃ የተወሰኑ ጉዳቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በህክምና ባለሙያዎች በኩል ለነገው ጨዋታ ይደርሳሉ የሚለውን ነገር ስናረጋግጥ መልሱን ነገ ብሰጥ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።


በጨዋታ መደራረብ በተጫዋቾች ላይ የሚኖረው ጫና…?

የጨዋታ መደራረብ መኖሩን ከግምት አስገባለሁ። ይህንን ፕሮግራም እኛ ያወጣነው ሳይሆን ከካፍ የመጣ ነው ይህንን ደግሞ አክብረን የመወዳደር ግዴታ አለብን መዝለል አንችልም። እንዲያውም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሊደነቅ የሚገባው ውድድሮችን አለመዝለሉ ነው።  ከዚህ ቀደም ብዙ ውድድሮች ይዘለሉ ነበር። አሁን ግን ምንም ዓይነት ውድድር እየተዘለለ አይደለም። ተጫዋቾች ደግሞ የመጣውን ውድድር የመጫወት ሀገራዊ ግዴታ አለባቸው። ስለዚህ በዚህ ቢወሰድ የተሻለ ነው። ጫናዎች ድካሞች ይኖራሉ ማንኛውም ተጫዋች ይህ እንደሚያጋጥመው ይታሰባል። ግን ለእነዚህ ተጫዋቾች በቂ የማገገሚያ ጊዜ በመስጠት ማስኬድ የአሰልጣኝ ሥራ ነው። ከ20 ዓመት በታች ቡድን ለኦሎምፒክ ማንን ነው የምጠቀመው የሚለውን እየሠራን ነው ፤ የጨዋታ ድግግሞሽ መኖሩ ተጫዋቾቹ ወጣት ከመሆናቸው አንፃር በጨዋታ ብዛት ልምድ እንዲያገኙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።