የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጨማሪ አጋር አግኝቷል

ሁለገብ ኦንላይን ሶሎሽንስ (Hulu Sport Betting) ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ጋር ለቀጣዩቹ ሁለት ዓመታት የሚዘልቅ የአጋርነት ስምምነትን ዛሬ ከሰዓት በይፋ ተፈራርሟል።

ዛሬ ከቀትር በኋላ በራማዳ ሆቴል በተካሄደው በዚህ የፊርማ ስነስርዓት በሁለገብ ኦንላይን ሶሎሽንስ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ይትባረክ ካሳሁን እና አክሲዮን ማህበሩን ወክለው በተገኙት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ መካከል ተፈፅሟል።

መርሃግብሩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፈ ሲሆኑ በንግራራቸው መግቢያም አክሲዮን ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እግርኳሳችን ሀብት ማመንጨት እንደሚችል ያረጋጡ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፤ ከሁለገብ ኦንላይን ሶሉሽንስ ጋር ስለተፈረመው የአጋር ስምምነት ዝርዝር ሀሳቦችን አንስተዋል።

በማብራሪያቸው የአጋርነት ስምምነቱ በዋነኝነት ሁለት ጥቅሎችን ያቀፈ መሆኑን አንስተው የመጀመሪያው ጥቅል ሁሉገብ ሶሉሽንስ ከቀጣይ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ለሊጉ ይፋዊ የመጫወቻ ኳሶችን የሚያቀርብ ሲሆን ሁለተኛው ጥቅል ደግሞ የውድድር አመራሮች ፣ ኳስ አቀባዮች ፣ የህክምና ባለሙያዎች እና የካሜራ ባለሙያዎች በጨዋታ ዕለት የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ አልባሳትን ተቋሙ የሚያቀርብ ይሆናል።

በማጠቃለያቸው አክሲዮን ማህበሩ በቀጣይም ከሌሎች ሀገር በቀል ተቋማት ጋር ለመስራት በራቸው ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል።

በማስከተል ንግግር ያደረጉት አቶ ይትባረክ ካሳሁን የሁለገብ ኦንላይን ሶሉሽንስ የቦርድ ሰብሳቢ ሲሆን በንግግራቸውም ተቋማቸው በስፖርት ውርርድ ዘርፍ የካበተ ልምድ ያለው ተቋም ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ደግሞ የተለያዩ ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በዋነኝነት ስለዛሬው ስምምነት መነሻም ሲያስረዱ ፕሪምየር ሊጉ ብዙ ድጋፎችን የሚሻ መሆኑን አንስተው በተለይም ከሎጀስቲክ ጋር ያለበትን ችግር ለመቅረፍ በማለም ይህን ስምምነት ስለማድረጋቸው አንስተው ከሁለቱ ጥቅሎች ባለፈ በቀጣይ ሊጉን ይበልጥ ለማነቃቃት ደጋፊዎችን አሳታፊ የሆኑ ተከታታይነት ያላቸው ሁነቶችን ለማዘጋጀት ስለመታሰቡ አንስተዋል።

በቀጣይነትም ለፕሪምየር ሊጉ ሆነ ለእግር ኳሳችን የሚሆኑ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ሌሎች ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንም ለማስተዋወቅ እንደሚተጉ ገልፀዋል።

በሁለቱ አካላት አመራሮች በኩል በተፈረመው የአጋርነት ሰነድ የቀጠለው መርሃግብሩ በማስከተልም ከቀጣይ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በሊጉ ጨዋታዎች ላይ ጥቅም ላይ የምትውለው የሊጉን አዲሷን ይፋዊ የሊጉ ኳስም ርክክብ ተደርጓል።

የመርሃግብሩ የመጨረሻ ክፍል የነበረው በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ጥያቄዎች ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ስምምነት ስለሚያጠቃልላቸው ሌሎች ጉዳዮች ለተነሳውን ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ክፍሌ ስምምነቱ በዋነኝነት በሁለት ዓመታት ውስጥ ስድስት ሚልዮን የሚገመት የዓይነት ድጋፍ እንዲሁም በገንዘብ ደግሞ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ውጭ አምስት ሚልየን ብር ለማህበሩ እንደሚያስገኝ የገለፁ ሲሆን ሌላው ክለቦች በተመሳሳይ መስክ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር እያደረጉ ካሉት ስምምነት አንፃር እንዴት ይቃኛል በሚል ለተነሳውም ጥያቄ ሲመልስ ይህ ስምምነት አክሲዮን ማህበሩን እንደ አወዳዳሪነቱ በበላይነት በሚያስተባብራቸው አካላት እና ሁኔታዎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን መሆኑን አንስተው አክሲዮን ማህበሩ በክለቦች በሚያደርጓቸው ስምምነቶች ላይ ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የመግባት ሆነ ጫና የማሳደር ፍላጎት የሌለው መሆኑን አንስተው ይህ ጉዳይ ከዛ አግባብ አንፃር መታየት እንዳለበት ገልፀዋል።