የዋልያዎቹ የማጣሪያ ጨዋታዎች የት ይደረጋሉ ?

በ 2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በሦስት ቀናት ልዩነት ሁለት የማጣሪያ ጨዋታ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎቹን የት እንደሚያደርግ ታውቋል።

በአሜሪካ ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ የጣምራ አዘጋጅነት የ 2026 የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳታፊዎቹን ቁጥር ወደ 48 ከፍ በማድረግ አፍሪካን የሚወክሉ ሀገራትንም ወደ ዘጠኝ ማሳደጉ ይታወቃል።

በምድብ 1 የተመደበችው ኢትዮጵያ ረቡዕ ሕዳር 5 ከ ሴራሊዮን እና ቅዳሜ ሕዳር 8 ከቡርኪናፋሶ ጋር ለምታደርጋቸው ጨዋታዎች ሀገራችን ውስጥ የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታውን ከሀገር ውጪ ለማድረግ በመገደዱ ሁለቱን የማጣሪያ ጨዋታዎች ሞሮኮ ላይ እንደሚያደርግ ታውቋል።

ሁለቱንም የመጀመሪያ ተከታታይ ጨዋታዎቹን ባለ ሜዳ ሆኖ የሚጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ካዛብላንካ በሚገኘው የመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም እንደሚያደርግ የሴራሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ ያደረገ ሲሆን ሁለተኛው የቡርኪና ፋሶ ጨዋታም በዛው ስታዲየም እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በዚህ ቀደም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ በዚሁ ስታዲየም ማድረጓ ይታወሳል።