መረጃዎች| 14ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

ሀምበሪቾ ከ ሀድያ ሆሳዕና

ተመሳሳይ ነጥብ አስመዝግበው በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታታይ ደረጃዎች ይዘው የሚገኙትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ግጥሚያ ይሆናል።

በመጨረሻው ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ተለያይተው የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ነጥባቸውን ያስመዘገቡት ሀምበሪቾዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ሀድያን ይገጥማሉ። ሀምበሪቾዎች በአጨዋወት ረገድ በየጊዜው መሻሻሎች ቢያሳዩም ነጥባቸውን ከፍ ማድረግ አልቻሉም። ቡድኑ አዳማን በገጠመበት ጨዋታ ምንም እንኳ ሁለት ግቦች ቢያስቆጥርም ከሌሎች ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ተቀዛቅዞ ታይቷል።

በጨዋታውም እንደሌላው ጊዜ በተመሳሳይ በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን የመቆጣጠር ችግር ተስተውሎባቸዋል። ቡድኑ በሦስቱም ሳምንታት አራት ግቦች አስቆጥሮ ከፍተኛ ግቦች በማስቆጠር በአራተኛ ደረጃነት ቢቀመጥም በተቃራኒውም ከፍተኛ የግብ መጠን ካስተናገዱ ሁለት ክለቦች አንዱ ነው። አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በነገው ጨዋታ እንደተለመደው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ይቸገራሉ ተብለው አይጠበቁም። ሆኖም ከጥሩ ሜዳ እንቅስቃሴ ባለፈ ውጤታማ የሚያደርጋቸውን አጨዋወት ይዘው መግባት ግድ ይላቸዋል። በተለይም በቡድኑ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚታየውን በሁለተኛው አጋማሽ የአካል ብቃት መውረድ መላ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።

ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈቶችና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ሀድያዎች እንደተጋጣሚያቸው በተመሳሳይ በመጨረሻው የአቻ ውጤት አስመዝግበው ወደ ጨዋታው ይገባሉ። ቀጥተኛ አጨዋወት መርጠው ጨዋታዎቻቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙት ሀድያዎች በአማካዮቹ ሽፋን የሚሰጠው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ቢኖረውም ውጤታማ ያልሆነው የአጥቂ ክፍሉ የቡድኑ ደካማው ጎን ነው።
በመጀመርያው ሳምንት ላይ መቻል ላይ ሁለት ግቦች ካስቆጠሩ በኋላም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ አለማስቆጠራቸው አንዱ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በነገው ጨዋታ የአጨዋወት ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም በዳዋ ሆቴሳ ጉዳይ ምክንያት የአጥቂ ክፍሉን በመምራት ላይ የሚገኘውንና በመጨረሻው ጨዋታ ደካማ እንቅስቃሴ ባደረገው ሬችሞንድ አዶንጎ ምትክ ወደ ሌላ የአጥቂ አማራጭ ያማትራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሀምበሪቾ በኩል ኤፍሬም ዘካርያስ በጉዳት አይሰለፍም የአማካዩ ብሩክ ቃልቦሬ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ሳሙኤል ዮሐንስ እና ዳዋ ሆቴሳ በጉዳት ምክንያት ቡድናቸውን አያገለግሉም።

ዋና ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመራዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

ከሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤቶች አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ እና የሊጉ ጠንካራው የአጥቂ ጥምረት ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ 12:00 ላይ ይጀምራል።

ከሦስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦች ሰብስበው ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ውጤታማው አጀመማመር ለማስቀጠል አዳማን ይገጥማሉ። ጊዮርጊሶች በሊጉ አስፈሪ የአጥቂ ጥምረት ካላቸው ቡድኖች ይጠቀሳሉ በሦስቱም ሳምንታት በየጨዋታው አማካይ ሦስት ግቦች እያስቆጠሩ ማሸነፋቸውም የዚህ ማሳያ ነው። ዘጠኝ ግቦች ያስቆጠረው ቡድኑ የሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ ቡድን ነው። በአመዛዡ ይበልጥ መስመሮችን ተጠቅመው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሚሞክረው ቡድኑ በአጨዋወቱ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥሯል። አብዛኞቹ ግቦች ያስቆጠሩበት መንገድም በተጠቀሰው አጨዋወት ነው።

ፈረሰኞቹ በጥሩ የማሽነፍ መንገድ ይገኛሉ፤ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይም ሁለቴ ከመመራት ተነስተው ጨዋታውን አሸንፈው መውጣታቸውንም የቡድኑ የሥነ-ልቦና ከፍታ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቅያሪዎች አሁንም በውጤታማነታቸውን ቀጥለዋል።

ከሦስት ጨዋታዎች ሁለት አቻና አንድ ድል አስመዝግበው በሊጉ ሽንፈት ያላስተናገዱት አዳማዎች በአምስት ነጥቦች በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ይበልጥ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚታትር ቡድን ያሳዩን አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በተለይም የአማካይ ክፍላቸው ላይ ለውጥ ካደረጉ በኋላ በተሻለ መንገድ የግብ ዕድሎች የሚፈጥር ቡድን አሳይተውናል።
በዚህ ሂደትም የአሰልጣኙ ውጤታማ ቅያሬዎችም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በሁለት ውጤታማ ቅያሬዎች ውጤት ይዘው ወጥተዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን በመጨረሻው ሳምንት አቻ ቢለያይም ከዚህ ቀደም ዋነኛ የቡድኑ ችግር የነበረው የማጥቃት አጨዋወት ብዙ ተስፋ ሰጪ መሻሻሎች ያሳየበት ነበር። በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በየጨዋታው 0.6 ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የአዳማ ተከላካይ ክፍል እና ግቦችን ማስቆጠር ላይ የማይሰንፈው እና በየጨዋታ በአማካይ ሦስት ግቦች ያስቆጠረው ጠንካራው የጊዮርጊስ የአጥቂ ክፋል የሚያደርጉት ፍልምያም ጨዋታውን ይበልጥ አጓጊ ያደርገዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም የቢንያም በላይ ግልጋሎት አያገኝም በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ከቅጣትና ጉዳት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 42 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ 23 ጊዜ ድል ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 56 ግቦችን ሲያስቆጥር 7 ጨዋታዎችን በድል የተወጣው አዳማ ከተማ ደግሞ 28 ግቦችን አስቆጥሯል። ክለቦቹ 12 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ሐይለየሱስ ባዘዘው የጨዋታው ዋና ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።