መረጃዎች| 23ኛ የጨዋታ ቀን

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ ያካተተው የነገውን መርሀ-ግብር የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ

በአፍሪካ መድረክ ተካፋይ የነበሩትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ፍልሚያ የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ይሆናል።

አራት ጨዋታዎች አሸንፈው በአንድ ጨዋታ አቻ በመለያየት በአስራ ሦስት ነጥቦች በሊጉ አናት የተቀመጡት ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ። ፈረሰኞቹ ጠንካራ የማጥቃት ጥምረት አላቸው፤ በየጨዋታው በአማካይ 2.8 ግቦች ተጋጣሚው ላይ ያዘነበው ይህ ክፍል በአምስት ጨዋታዎች አስራ አራት ግቦች በማስቆጠር የሊጉ ቀዳሚ ነው። ይህንን የአጥቂ ክፍላቸውም የቡድኑ ዋነኛው ጠንካራ ጎን ነው። ሆኖም በነገው ዕለት በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደ መግጠማቸው የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም። ፈረሰኞቹ ለተከላካዩ ሽፋን በሚሰጡ ሁለት የተከላካይ አማካይ የሚጫወት ቡድን ነው፤ ሆኖም ጠንካራ የሚባል የመከላከል አደረጃጀት አላቸው ለማለት አያስደፍርም። ከአምስቱ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣታቸውና ስድስት ግቦች ማስተናገዳቸውም ለዚህ ማሳያ ነው። በነገው ዕለት ግን የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ እንደመግጠማቸው ከወትሮው ለየት ያለ የመከላከል ጥንካሬ ይዘው መግባት ይጠበቅባቸዋል።

ሁለት ድል፣ ሁለት አቻና አንድ ሽንፈት አንስተናግደው በስምንት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ላይ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ የተለያዩት ባህር ዳሮች ምንም እንኳ በጨዋታው በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥሩ ቢወጡም ውጤታማ የሚባል የማጥቃት ክፍል አላቸው። በርካታ ግቦች በማስቆጠርም ከነገው ተጋጣሚያቸው ጊዮርጊስ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃነት ተቀምጠዋል፤ በየጨዋታውም በአማካይ 1.8 ግቦች አምርተዋል። የጣና ሞገዶቹ በዋነኝነት በፈጣን ሽግግሮች ላይ የተመሰረተ አጨዋወት አላቸው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተሻጋሪ ኳሶች የማጥቅያ አማራጮቻቸው ለማስፋት ጥረት አድርገዋል። በጊዜ ሂደትም የቡድኑ የማጥቅያ መሳርያ ተገማች አለመሆኑ ለተጋጣሚዎች ፈታኝ አድርጎታል። ይህንን ተከትሎም በነገው ዕለት በተጠቀሱት ሁለት መንገዶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይገመታል። በመጀመርያዎቹ ሦስት ሳምንታት የተጋጣሚን ጥቃት ለመመከት ሲቸገር የተመለከትነው የባህርዳር ከተማ የተከላካይ ክፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች አሳይቷል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር መውጣቱም የመሻሻሉ አንድ ምልክት ነው። በነገው ዕለት ግን ግቦችን ለማስቆጠር የማይሰንፈው የሊጉን ጠንካራ የማጥቃት ጥምረት እንደመግጠሙ ከፊቱ ትልቅ ፈተና ይጠብቀዋል።

የቡድን ዜናን በተመለከተ ጉዳት ላይ የነበሩት የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ቢንያም በላይ እና ዳግማዊ አርአያ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ተመልሰዋል፤ በነገው ጨዋታም የሚያጡት ተጫዋች የለም። በጣና ሞገዶቹ በኩልም በተመሳሳይ በቅጣም ሆነ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፈው ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ ስምንት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈው አራት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ስምንት ባህር ዳር ከተማ ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ጨዋታው ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሐል ዳኝነት ሲመራው፤ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሙሉነህ በዳዳ ረዳቶች፤ ሔኖክ አበበ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተሰይሟል።

ሲዳማ ቡና ከ ሀድያ ሆሳዕና

የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረጉ ሁለት ክለቦች የሚያገናኘውን ቀጣዩ ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይከናወናል።

ሦስት ሽንፈት ፣ አንድ ድል እና አቻ በእኩሌታ አስመዝግበው አራት ነጥቦች በመሰብሰብ በአስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች
ከአሰልጣኝ ለውጥ በኋላ የመጀመርያው የሊግ ጨዋታቸው ያደርጋሉ። አሰልጣኝ አረጋዊ ወንድሙ በነገው ዕለት ይዘውት የሚገቡትን አጨዋወት ለመገመት ብያዳግትም ቡድኑ በኢትዮጵያ ዋንጫ በአዳማ ከተማ በሰፊ የግብ ልዩነት በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ የታዩበትን ግልፅ የመከላከል ድክመቶች ግን አሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል። ከዚ ቀደም በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ያልተቆጠረበትና ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች በአንፃራዊነት የተሻለ የነበረው ክፍል ወደ ቀድሞ ጥንካሬው መመለስም የአሰልጣኙ ቀዳሚ የቤት ስራ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ከዚ በተጨማሪ ሲዳማዎች ከአምስት በሦስቱ ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የወጣ ደካማ የማጥቃት ክፍል አላቸው። ይህንን የቡድኑ ዋነኛ የግብ ማስቆጠር ችግር መቅረፍም ሌላው ትልቁ የቤት ስራቸው ነው። ቡድኑ አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ከጉዳት መልስ ማግኘቱ ጥሩ ዜና ነው፤ ተጫዋቹ በነገው ጨዋታ ተጠባባቂ ሆኖ የሚጀምርበት ዕድልም የሰፋ ነው።

እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በጊዝያዊ አሰልጣኝ እየተመሩ ወደ ጨዋታው የሚገቡት ሀድያዎች በሦስት ጨዋታዎች የአቻ በሁለት ደግሞ ሽንፈት በማስተናገድ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ሀድያዎች በመጀመርያው ሳምንት መቻል ላይ ሁለት ግቦች ካስቆጠሩ በኋላ ለተከታታይ አራት ሳምንታት ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኗቸዋል። ክለቡን በጊዝያዊነት የተረከቡትና በአዲስ አበባ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ ቡድኑን የመሩት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰም ጥቂት የግብ ዕድሎች የፈጠረውና መከላከል ላይ ያተኮረው የቀደመ የቡድኑ አጨዋወት ከመቀየር በዘለለ ደካማው የአጥቂ ክፍል ላይ ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሀድያዎች ሦስት ተከታታይ የባዶ ለባዶ ውጤቶች አስመዝግበው ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣት ቢችሉም፤ ሚዛኑ ወደ መከላከሉ ላይ ያደላው አጨዋወታቸው በቂ የግብ ዕድሎች አልፈጠረላቸውም። ቡድኑ ወደ ግብ ማስቆጠሩ ሆነ ወደ ማሸነፍ መንገድ እንዲመለስም የቡድኑ ሚዛን ማመጣጠን ጊዜ የማያስፈልገው ውሳኔ ነው።

በሲዳማ ቡና በኩል አጥቂው ይገዙ ቦጋለ ከጉዳት ቢመለስም በዚህ ጨዋታ የመግባቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፤ ፊሊፕ አጃህ እና ገዛኸኝ ባልጉዳ ግን በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው አይደርሱም። በሀድያ ሆሳዕና በኩል ሔኖክ አርፊጮና ሳሙኤል ዮሐንስ በጉዳት አይኖሩም በረከት ወልደዮሐንስ ግን ከቅጣት ይመለሳል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ስምንት ጨዋታዎች አድርገዋል። ሁለቴ ነጥብ ሲጋሩ 15 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና አራት ፣ 8 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ድሎችን አስመዝግበዋል።

ዳንኤል ይታገሡ ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ሲመራ ሲራጅ ኑርበገን እና ዘመኑ ሲሳይነው ረዳቶች ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ በአራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።