ከፍተኛ ሊግ | የ4ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ ሞጆ ከተማ ፣ ካፋ ቡና ፣ አዲስ አበባ ከተማ ፣ ኦሜድላ፣ ንብ እና የካ ክ/ከተማ ድል አድርገዋል።

ምድብ 1

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ስልጤ ወራቤ እና ሞጆ ከተማን አገናኝቷል። በጨዋታው ጅማሮ ላይ ስልጤ ወራቤ ወደፊት በመሄድ ያገኘውን የግብ እድል ማቲያስ ኤሊያስ ወደ ግብ በመላክ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በጨዋታው  ሞጆ ከተማ ኳስን መሠረት አድርጎ በጥሩ አጨዋወት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አርጓል። በአንፃሩ ስልጤ ወራቤ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርግ ተመልክተናል። በ28ኛው ደቂቃ ሞጆ ከተማ ያደረገው የግብ ሙከራ በኑራ ሀሰን አማካኝነት ሞክሮ ለጥቂት የግቡን አግዳሚ መልሶ ወደ ውጪ ወቷል። በ45ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ተጫዋቹ ማቲያስ ኤሊያስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አጋማሹም ተጠናቆ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ፈጣን እና የተሻለ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት አጋማሽ ነው ። ሁለቱም ቡድኖች ውጤት ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በ63ኛው ደቂቃ የሞጆ ከተማው ተጫዋች የሆነው ፍቃዱ ባርባ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።  ይህንንም ተከትሎ ስልጤ ወራቤ በኳስ ቁጥጥር ተሽሎ ተገኝቷል። በአንፃሩ ሞጆ ከተማ በተወሰደበት የተጫዋች ብልጫ  ወደኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል። በ68ኛው ደቂቃ የሞጆ ከተማ ተጫዋች የሆነው ያሬድ ሽመልስ ከመስመር ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሯል። ብዙም ሳይቆይ በ76ኛው ደቂቃ ማቲያስ ኤሊያስ የተጨራረፈ ኳስ በማግኘት ለስልጤ ወራቤ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታው በዚው ቀጥሎ መደመኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ሞጆ ከተማ ያገኘውን የመጨረሻ የግብ እድል በብርሀኑ ዋልቂቶ አማካኝነት አስቆጥሮ ቡድኑ ጨዋታውን በድል እንዲወጣ አርጓል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኮልፌ ክ/ከተማን እና ንብ ክለብን አገናኝቷል። በጨዋታው ኮልፌ ክ/ከተማ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም በትንሽ ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አርገዋል። በአንፃሩ ንብ ኳስን መሠረት በማድረግ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህም አጨዋወት በ22ኛው ደቂቃ በኮልፌ ክ/ከተማዎች ተከላካይ የአቋቋም ስህተት የተገኘውን ኳስ የንብ የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ናትናኤል ሰለሞን ወደ ግብ መቀየር ችሏል። አጋማሹም በዚው ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ቅያሪ አድርገው የተሻለ እንቅስቃሴ ለማረግ ጥረት አድርገዋል። በ56ኛው ደቂቃ ከርቀት የተሞከረውን ሙከራ የንብ ግብ ጠባቂ የሆነው ሶፎኒያስ ሰይፉ በድንቅ ብቃት አድኖታል። በዚው ሁኔታ ቀጥሎ ኮልፌ ክ/ከተማ ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ምንም ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ጨዋታውም በዚው ውጤት ተጠናቋል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን እና ቤንች ማጂ ቡናን አገናኝቷል። የቤንች ማጂ ቡና የበላይበት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድል በመፍጠር ተሽለው ተገኝተዋል። በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግብ በማድረስ የግብ እድል ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በ34ኛው ደቂቃ ላይ በአከራካሪ ሁኔታ የፀደቀው ግብ የቤንች ማጂ ቡና የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ወንድማገኝ ኪራ ከበረኛ የተተፋውን ኳስ መልሶ በመምታት ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባ ከተማ ጠንክሮ በመግባት የተሻለ እንቅስቃሴ አርጓዋል። በዚህም ሁኔታ በ54ኛው ደቂቃ አዲስ አበባ ከተማ ተጫዋች ላይ በተሰራ ጥፋት ቢንያም ተክሌ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ መቀየር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማ ተጭኖ መጫወት ችሏል። በ65ኛው ደቂቃ ቢንያም ፀጋዬ ተጨማሪ ግብ ለአዲስ አበባ ከተማ አስቆጥሯል። ቤንች ማጂ ቡና በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሆኖም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በዚው ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።

ምድብ 2

የምድቡ የመጀመሪያ የሆነው የየካ ክፍለ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ ጨዋታ ቀዳሚው ነበር። በአሰልጣኝ ባንተይርጋ ጌታቸው የሚመመሩት የመዲናይቱ ተወካይ የካ ክፍለ ከተማ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ መገባደጃ 45ኛ ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ጌታሁን አየለ ከመረብ ባገናኛት ብቸኛ ጎል ጨዋታውን 1ለ0 አሸንፈው ወጥተዋል።

ከቀትር መልስ ልክ 8፡00 ሲል ሁለቱን የአዲስ አበባ ክለቦች ኦሜድላ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ጥሩ ፉክክርን አስመልክቶን የተናቀቀ ነበር። በአንጋፋው አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባ የሚመሩት ኦሜድላዎች በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ አቀራረብ በፍጥነት በሚደረግ የሽግግር አጨዋወት ጫናን ፈጥሮ ለመጫወት የሞከሩት ገና ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ነበር። በእንቅስቃሴ በኦሜድላ ይበለጡ እንጂ የሚያገኙትን ኳስ በቀጥተኛ የጨዋታ ሂደት ፈታኝ ከመሆን ያልቦዘኑት አዲስ ከተማዎች የኋላ መስመራቸው ከሚታይበት መላላት አኳያ በተጋጣሚው ጫና ውስጥ ሲገባ ተስተውሏል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ኦሜድላዎች በኤፍሬም ቶማስ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ከጨዋታው ውጪ ከተባለ ከሁለት ደቂቃዎች መልስ የመሪነት ግባቸውን በአንዋር መሐመድ አማካኝነት አግኝተው አጋማሹ በ1ለ0 ውጤት ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ክፍተታቸውን በይበልጥ ለማረም የሞከሩት ኦሜድላዎች በተቃራኒው በእጅጉ ተሻሽለው በመስመር አጨዋወት አደገኛ ሆነው በቀረቡት አዲስ ከተማዎች 50ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ሊያስተናግዱ ተገደዋል። ተቀይሮ የገባው ማሙሽ ደባሮ ቢኒያም ትዕዛዙ ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ አሰፋ ከመረብ በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን ወደ ጨዋታ መልሷል። ወጥነት በሌለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው የሚያገኙትን ኳስ ፈጠን በማለት ወደ ጎልነት ለመለወጥ ሲጥሩ የሚታዩት ኦሜድላዎች 56ኛው ደቂቃ ከቀኝ በረጅሙ ከቅጣት ምት የደረሰውን ኳስ ዘካሪያስ በየነ በማስቆጠር ዳግም ቡድኑ መሪ አድርጓል። ጎል ለማስቆጠር አስፈሪ ሲሆኑ ይታይ እንጂ የኋላ ክፍላቸው የሳሳባቸው ኦሜድላዎች 66ኛው ደቂቃ የአዲስ ከተማው አማካይ ሠለሞን ጌዲዮን ከቀኝ ወደ ውስጥ እየነዳ ገብቶ የሰጠውን ኳስ ቅዱስ ተስፋዬ ጎል አድርጎት ቡድኑን 2ለ2 ማድረግ ችሏል። የጨዋታውን የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች አሸንፎ ለመውጣት በብርቱ የታገሉት ኦሜድላዎች 84ኛ ደቂቃ ላይ አምበሉ ቻላቸው ቤዛ ከቀኝ በኩል ያሻማውን ኳስ አብዱሰላም አማን በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር በመጨረሻም ጨዋታው በኦሜድላ 3ለ2 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ሆኗል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሆነው የደብረብርሃን እና ካፋ ቡና ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ ድራማዊ ጎል ካፋ ባለ ድል ሆኖ ወጥቷል። ተመጣጣኝ መልክ የነበረውን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ነገር ግን በወጥነት የደብረብርሃን የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ጎልቶ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሙከራዎች ረገድ ደካማውን አጋማሽ ታዝበናል። ደብረብርሃኖች ከመስመር መነሻቸውን አድርገው በተጫወቱበት አጋማሽ 19ኛው ደቂቃ በአብዱልመጅድ ሁሴን አማካኝነት ያለቀለትን ዕድል አግኝተው ግብ ጠባቂው ቅዱስ ዳኜ ያዳነባቸው የቡድኗ ጠጣሯ ሙከራ ሆናለች። በእጅጉ ብዙ ክፍተቶች ቢታይባቸውም የሚያገኙትን ዕድል በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም የሚታትሩት ካፋ ቡናዎች የተጫዋች ለውጥን ገና በጊዜ ካደረጉ በኋላ በያቤፅ ፍሬው አማካኝነት ሁለት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በሁለተኛ አጋማሽ በድጋሚ የተመለሰው ጨዋታው በእንቅስቃሴ የደብረብርሀን የበላይነት ይታይበት እንጂ ካፋ ቡናዎችም በሒደት ጥሩ ለመጫወት የሞከሩበትም ሆኗል። የጎል ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር በእጅጉ ውስንነቶች ያየሉበት ሁለተኛው አጋማሽ ደብረብርሃኖች 55ኛው ደቂቃ ላይ አብርሃም መለሠ ከግብ ጠባቂ ተገናኝቶ መጠቀም ያልቻለበት እና ዑስማን መሐመድ ደግሞ 60ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ጠርዝ የመታውን ቅዱስ ዳኜ ያዳነበት ተጠቃሾቹ የቡድኑ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ናቸው። የጨዋታውን የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች የተጫዋች ለውጥን አከታትለው ካደረጉ በኋላ መሻሻሎች የታየባቸው የአሰልጣኝ ራህመቶ መሐመዱ ካፋ ቡና 84ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው ታዳጊው ያልፋል ደነቀ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው 1ለ0 በሆነ ውጤት በመጨረሻም አሸንፈው ወጥተዋል።