ሪፖርት | ነብሮቹ ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ያለ ግብ ተለያይተዋል

ምሽት ላይ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

በምሽቱ መርሐግብር ሲዳማ ቡና እና ሀዲያ ሆሳዕና ሲገናኙ በሮድዋ ደርቢ በሀዋሳ ከተማ 1ለ0 የተሸነፉት ሲዳማዎች ያኔ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መክብብ ደገፉ ፣ በዛብህ መለዮ እና ጸጋዬ አበራ በ መሐመድ ሙንታሪ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና ቡልቻ ሹራ ምትክ ገብተዋል። በነብሮቹ በኩል ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ያለ ግብ ከተለያየው ስብስባቸው ካሌብ በየነ ፣ አስጨናቂ ጸጋዬ ፣ ብሩክ ማርቆስ እና ከድር ኩሊባሊን ብቻ በድጋሚ ተጠቅመዋል።

12፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እጅግ የተቀዛቀዘ ነበር። ሲዳማዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በርካታ ቅብብሎችን በማድረግ ዝግ ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ሀዲያዎች በአንጻሩ በጥቂት ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ለመድረስ ጥረት አድርገዋል።

ሀዲያዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 3ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በጥሩ ቅልጥፍና ሲያስወጣበት ያ ኳስም በግራ መስመር ከማዕዘን ተሻምቶ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ደስታ ዋሚሾ ያደረገውን ሙከራ ጸጋዬ አበራ በግንባሩ በመግጨት መልሶበታል።

ሲዳማዎች በአጋማሹ ብቸኛውን የጠራ የግብ ዕድላቸውን 21ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ብርሃኑ በቀለ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ ሲመልሰው ኳሱን ሳይዘጋጅ ያገኘው ጸጋዬ አበራ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ፉክክር ይደረግበት እንጂ በሁለቱም ሳጥን ላይ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረገበት በዘለቀው ጨዋታ ሀዲያዎች የተሻለውን ተጨማሪ የግብ ዕድል 40ኛው ደቂቃ ላይ መፍጠር ችለው ነበር። ተመስገን ብርሃኑ በድንቅ ሩጫ በሳጥን የቀኝ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ለዳዋ ሆቴሳ አቀብሎት ዳዋም ነጻ ሳይሆን የሞከረውን ኃይል የለሽ ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በቀላሉ ይዞበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል የጨዋታው የተሻለ  ለግብ የቀረበ ሙከራ 56ኛው ደቂቃ ላይ በነብሮቹ አማካኝነት ሲደረግ ብሩክ ማርቆስ ከመለሰ ሚሻሞ በተመቻቸለት ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በድንቅ ብቃት አስወጥቶበታል።

በሲዳማዎች በኩል በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው አጥቂው ይገዙ ቦጋለ በ ጸጋዬ አበራ ተቀይሮ ወደ ሜዳ መመለሱ መልካም ዜና ቢሆንም ሌሎች ቅያሪዎችንም ያደረጉት ሲዳማዎች  በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ግን ፈታኝ መሆን አልቻሉም ነበር። ሆኖም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረሱ በኩል ይበልጥ እየተጋጋሉ የሄዱት ሀዲያዎች 69ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ማርቆስ 73ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተመስገን ብርሃኑ ከዳዋ ሆቴሳ በተቀበሉት ኳስ ባደረጉት ሙከራም የሲዳማን ሳጥን መፈተን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በማጥቃት እንቅስቃሴው ብልጫ የነበራቸው ሀዲያዎች 84ኛው ላይም ተጨማሪ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ያገኘው መለሰ ሚሻሞ ያደረገውን ሙከራ የጨዋታው ኮከብ የነበረው የሲዳማው ግብ ጠባቂ መክብብ ደገፉ መልሶበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል። ውጤቱም ለሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ አራተኛ የ 0-0 ውጤት ሆኖ ተመዝተመዝግቧል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሲዳማው አሰልጣኝ አረጋይ ወንድሙ የተጋጣሚያቸውን አቀራረብ ማፍረስ ቢችሉም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የሚሄዱበት መንገድ ጥራት የጎደለው እንደነበር ሲገልጹ የሀዲያ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ጨዋታው ባሰቡት ልክ እንዳልሄደ እና በሁለተኛው አጋማሽ ለማስተካከል እንደሞከሩ ሲናገሩ የገቡበትን የ 4-4-2 አሰላለፍ ከተጫዋቾቹ አቅም አንጻር ወደ 4-3-3 ለመቀየር መገደዳቸውን በመጠቆም ውጤቱም በቂ እንደሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።