ከፍተኛ ሊግ | የ5ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

አምስተኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በሁለቱ ምድቦች ያስተናገዳቸው ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ በመሸናነፍ ተጠናቀዋል።

ምድብ ሀ

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ኮልፌ ቀራኒዮ በኳስ ቁጥጥር እና አጫጭር ኳስ ላይ ተሽሎ ተገኝቷል። በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ረጃጅም ኳስን በተደጋጋሚ በመጠቀም የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚው አጨዋወት ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴን ተመልክተናል።  32ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋች ከመስመር ያሻገረውን ኳስ መሳይ ሰለሞን ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል። አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአጨዋወትም ሆነ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ተሽለው ተገኝተዋል። በአንፃሩ ኮልፌ ቀራኒዮ ከመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብለው ታይተዋል። በ62ኛ ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋች የሆነው ናትናኤል ሰለሞን ያገኘውን የግብ ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞ ሲያስቆጥር ጨዋታውም በዚሁ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል። ነጥባቸውን 15 ማድረስ የቻሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመቶ ፐርሰንት ድል ምድቡን መምራት ቀጥለዋል።

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው የሞጆ ከተማ እና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ነበር። አራት ግቦችን የተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው ጅማሬ ላይ  ሞጆ ከተማ ጥሩ የሚባል አጨዋወትን ተመልክተናል። ይህንንም ተከትሎ ሞጆዎች በፈጠሩት ጫና  በ20ኛው ደቂቃ በኑሪ ሁሴን ድንቅ ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ተጫውተዋል። በዚሁ አጨዋወታቸው ቀጥለው በ41ኛው ደቂቃ ቢኒያም ተክሌ ለአዲስ አበባ ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማ በድጋሚ ጫና ፈጥረው ከ2 ደቂቃ በኋላ በ43ኛው ደቂቃ ቡይ ኮዌት ግብ አስቆጥሯል። የተነቃቃው አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ 45+2ኛ ደቂቃ ላይ ውብሸት ክፍሌ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ሞጆ ከተማን ተስፋ ማስቆረጥ ችሏል። አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ አዲስ አበባ ከተማ ብልጠት በሞላው አጨዋወት ያገኙትን የግብ ልዩነት ለማስጠበቅ ተጫውተዋል። ሞጆ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ማስቆጠር ተስኖት ጨዋታው ከዕረፍት በፊት በተቆጠሩ ግቦች 3ለ1 መጠናቀቅ ችሏል። አዲስ አበባዎች በ11 ነጥቦች መሪውን መከተላቸውን ቀጥለዋል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቤንችማጂ ቡናን ከሀላባ ከተማ ያገናኘ ጨዋታ ነበር።  በአጋማሹ መጀመሪያ ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ተመልክተናል። ሀላባ ከተማ ወደ ኋላ በማፈግፈግ እና ኳስን ለተጋጣሚ በመተው በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ቤንችማጂ ቡና ተጭነው ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ በ46ኛው ደቂቃ ቤንችማጂ ቡና በፈጣን ማጥቃት ወደ ሀላባ ከተማ የግብ ክልል በመሄድ በኢብራሂም ከድር አማካኝነት ግብ አስቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሀላባ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲያደረግ ተስተውሏል። ሆኖም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው በዚሁ የ1-0 ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።

የምድብ ‘ሀ’ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲከናወኑ 03:30 ላይ ይርጋጨፌ ቡና ከ ነቀምቴ ከተማ ፣ 05:30 ላይ ወልዲያ ከ ጅማ አባ ቡና ፣ 07:30 ላይ ጅማ አባ ጅፋር ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ እንዲሁም 09:30 ላይ ንብ ከ ስልጤ ወራቤ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይገናኛሉ።

ምድብ ለ

በምድብ ለ በተደረጉ በመጀመሪያ ቀን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ኦሜድላ ፣ ደብረብርሃን ከተማ እና ባቱ ከተማ ድል አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ‘ለ’ ሦስት ያህል ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን አራት ሰዓት ላይ በተደረገው መርሐግብር የካ ክፍለ ከተማ ከ ኦሜድላ ተገናኝተው ኦሜድላ በቻላቸው ቤዛ ብቸኛ ግብ አሸናፊ ሆኗል።

ብዙ የግብ ሙከራዎች ባልታዩበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄ በተሞላበት አጨዋወት መከላከልን የመረጡ በሚመስል መልኩ  አንደኛው አጋማሽ 0-0 በሆነ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ከመልበሻ ክፍል መልስ ኦሜድላ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል አካባቢ ኳስን ይዘው ሲገቡ ተስተውሏል።

በ60ኛው ደቂቃ ላይ የኦሜድላ አምበል ቻላቸው ቤዛ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ኦሜድላዎችን መሪ አድርጓል። የአቻነት ግብ አብዝተው በመፈለግ በመነቃቃት በመልሶ ማጥቃት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉት የካ ክ/ከተማዎች ጫና ፈጠረው መጫዎት ችለው የነበሩ ቢሆንም 65ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ አመሃ በተቃራኒ ቡድን ላይ በሠራው ጥፋት ከሜዳ በመወገዱ በጎደሎ ሲጫወቱ ስለነበር ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው 1ለ0 በሆነ ውጤት ሽንፈት አስተናግደዋል። በውጤቱ ኦሜድላ ነጥቡን 10 በማድረስ ወደ መሪዎቹ መጠጋት ችሏል።

7 ያህል ግብ በተቆጠረበት በ8 ሰዓቱ ጨዋታ ደብረብርሃን በምድቡ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ የቻለውን ሸገር ከተማን 4ለ3 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። አዝናኝ በነበረው በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ተሽለው የቀረቡት ደብረብርሃኖች በ21ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ተመትቶ ወደ ግብ በተቆጠረው በኡስማን መሀመድ ግብ መሪ መሆን ችለዋል።

ሸገሮች በ33ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የፊት መስመር ተጫዋች የሆነው ፋሲል አስማማው ባስቆጠራት ድንቅ ግብ አቻ መሆን የቻሉ ቢሆንም የመጀመሪያ አጋማሽ ሊያልቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዎች ሲቀሩ የብርሃኖቹ አምበል የተሻ ግዛው ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ዕረፍት 2-1 በሆነ ውጤት እየመሩ እንዲወጡ አስችሏቸዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ መሪነታቸውን ያጠናከረችዋን ግብ ሄኖክ አየለ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ወደግቢነት በመቀየር ብርሃኖቹን 3ለ1 እንዲመሩ ማድረግ ችሏል።

የምድቡ ተፎካካሪነታቸውን ለማስቀጠል ትልቅ ተጋድሎ ሲያደርጉ የተስተዋሉት ሸገሮች 67ኛው ደቂቃ ላይ ነብዩ ንጉሤ ባስቆጠራት ግብ የግብ ብልጫውን በማጥበብ 3ለ2 መሆን ችለዋል። ይሁን እንጂ ከወራጅ ቀጠና ፈቀቅ ለማለት ጨዋታውን ማሸነፍ ግድ የሆነባቸው ብርሃኖቹ በ75ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው በመስመር በኩል እየገፋ በመሄድ አክርሮ በመምታት ባስቆጠራት ግብ ድጋሚ መሪነታቸው በሁለት ግብ ልዩነት ማድረግ ችሏል።

ብዙ ግቦች በተቆጠሩበት በዚህ ጨዋታ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያደረገው የሸገር ከተማው ዘጠኝ ቁጥር ለባሽ ፋሲል አስማማው በ85ኛው ደቂቃ በርቀት መትቶ ግብ ቢያስቆጥርም ብርሃኖቹ 4-3 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። በውጤቱ ምንም ነጥብ ያልነበራቸው ደብረብርሃኖች የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ማሳካት ሲችሉ ሸገር ከተማ ቢያንስ ነጌሌ አርሲ ጨዋታውን እስኪያደርግ ምድቡን መምራት የሚችልበትን ዕድል አምክኗል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው በካፋ ቡና እና ባቱ ከተማ መካከል በተደረገው ፍልሚያ ባቱ ከተማ እስራኤል ሸጎሌ እና ወንደወሰን በለጠ ተቀይሮ በመግባት ባስቆጠሯቸው ግቦች 2ለ0 ማሸነፍ ችለዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ጥሩ እንቅስቃሴ ባልታየበት በዚህ ጨዋታ ባቱ ከተማዎች ብዙ ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አግኝተው ሳይጠቀሙ የቀሩ ሲሆን ካፋ ቡና በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችሎ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን በመቀየር ተሻሽሎ የገባው የባቱ ከተማ ቡድን በ62ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው በእስራኤል እሸቱ ላይ ሳጥን ውስጥ በተሠራው ጥፋት ፍጹም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን ራሱ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮ ባቱ ከተማን ቀዳሚ አደርጓል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊያልቅ ሦስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩም ተቀይሮ የገባው ወንድወሰን በለጠ በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ ወደተቃራኒ ግብ ክልል አካባቢ በመግባት ኳስን ከመረብ አገናኝቶ ባቱ ከተማ 2-0 አሸንፎ እንዲወጣ አስችሏል። ድሉን ተከትሎ ባቱዎች ነጥባቸው 5 በማድረስ ከሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ፈቀቅ ማለት ችለዋል።

የምድብ ‘ለ’ ጨዋታዎች ነገም ቀጥለው ሲከናወኑ 03:00 ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ ደሴ ከተማ ፣ 05:00 ላይ ቢሾፍቱ ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ ፣ 08:00 ላይ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ከ ቦዲቲ ከተማ እንዲሁም 10:00 ላይ ጋሞ ጨንቻ ከ ወሎ ኮምቦልቻ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ይገናኛሉ።