ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | አዲስ አበባ ከተማ ከመሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥቡን አስተካክሏል

በምድብ ‘ሀ’ 8ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው አዲስ አበባ ከተማ ፣ ቤንች ማጂ ቡና እና ጅማ አባቡና በጠባብ ውጤት አሸንፈዋል።

ረፋድ 3:30 ሲል የጀመረው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የሁለተኛ ቀን መርሐግብር ሀላባ ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በሀላባ ከተማ በኩል ኳስን በመያዝ ረገድ የተሻለ ሆኖ የግብ ሙከራ ላይ የተቀዛቀዘበትን እንቅስቃሴ አስመልክቶናል። በአንጻሩ አዲስ አበባ ከተማ ኳስን ከተጋጣሚ በመንጠቅ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። 37ኛው ደቂቃ ላይ የሀላባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ፎሳ ሴዴቦ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ከግብ ጋር ተገናኝቶ ማስቆጠር ሳይችል አባክኗል። አጋማሹም ያለ ምንም ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተሻሽለው የተገኙበት አጋማሽ ሆኗል። በ50ኛው ደቂቃ አዲስ አበባ ከተማ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ አማኑኤል አሊሶ ከጥልቀት በመነሳት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ይዞ ገብቶ በራሱ ጥረት ግሩም በሆነ አጨራረስ የጨዋታውን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ግቧ ከተቆጠረች በኋላ ሀላባ ከተማ የተጫዋች ቅያሪ አድርጎ ቡድኑን ለማነቃቃት እና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሆኖም የአዲስ አበባን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ማለፍ ተስኖታል። በ75ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ዝናቡ ደመረ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሀላባ ከተማ ግብ ጠባቂ የሆነው ሀብታሙ ከድር በአስደናቂ ሁኔታ ማዳን ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በአዲስ አበባ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን ወደ 18 በማሳደግ ከመሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ዕኩል በመሆን በግብ ልዩነት ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሐግብር ቤንችማጂ ቡና በጠባብ ውጤት አሸንፏል።

ቤንች ማጂ ቡናን ከወልዲያ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ቤንች ማጂ ቡና ከጨዋታው መጀመር አንስቶ በፈጣን የኳስ ቅብብል እና ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በ12ኛው ደቂቃ የቤንች ማጂ ተጫዋች የሆነው ሀሰን ሁሴን መሀል ሜዳውን አቆራርጦ የወልዲያ የግብ ክልል በመግባት ለቡድን ጓደኛው ዳግም ሰለሞን ተጫዋች ቀንሶ በመስጠት የተቀበለውን ኳስ በአስገራሚ አጨራረስ ዳግም ሰለሞን ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ቤንች ማጂ ቡና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የወልዲያን ግብ በተደጋጋሚ ሲያንኳኩ ተስተውሏል። በአንፃሩ ወልድያ ከተማ በመከላከሉም በማጥቃቱም ረገድ እጅጉን ወርደው አጋማሹን አጠናቀዋል። ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርም ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተሻሽሎ ለመቅረብ ጥረት አድርጓል። ቤንች ማጂ ቡና ኳስን በማንሸራሸር የጨዋታውን ፍጥነት ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። ቤንች ማጂ ቡና በ65ኛው ደቂቃ የኳስ ፍሰቱ እንደመጀመሪያው ግብ እንደተቆጠረበት ሁኔታ ሀሰን ሁሴን ኳስን ቀንሶ ለዘላለም በየነ የሰጠውን ኳስ በግቡ አግዳሚ ላይ አሳልፎ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ወልዲያ የመጨረሻውን 15 ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጫና መፍጠር የቻሉ ቢሆንም በቤንች ማጂ የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታውን በሽንፈት ደምድመዋል።


ቀን 7:30 ላይ በተደረገው የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን ከ ንብ አገናኝቷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጅማ አባ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና የንብ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተመለከትንበት አጋማሽ ሆኗል። በ15ኛው ደቂቃ የጅማ አባ ቡና ተጫዋች የሆነው እስጢፋኖስ ተማም ያገኘውን ኳስ ለጴጥሮስ ገዛኸኝ በጥሩ ሁኔታ በማቀበል ጴጥሮስ ገዛኸኝ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ  ጥሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ አጨዋወት እና ውጥረት የበዛበት አጋማሽ ሲሆን የግብ ሙከራም ብዙም ያልታየበት አጋማሽ ሆኗል። ጅማ አባ ቡና የወሰደውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ መከላከልን ምርጫው አድርጎ የሚያገኘውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ንብም ግብ ለማስቆጠር በሙሉ አቅማቸው የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በጅማ አባ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።