የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የማያገኙት ሣምንታት ተለይተዋል

የዲኤስቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የማያገኙት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የትኞቹ እንደሆኑ ታውቀዋል።

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  የስምንተኛ ሣምንት ጨዋታዎችን አጠናቅቆ የዘጠነኛውን ሣምንት ከቀጣይ ሣምንት ሐሙስ ታኅሣሥ 25 ቀን ጀምሮ እንደሚያደርግ መርሐግብሩ ይጠቁማል። ቅዳሜ ታኅሣሥ 20 በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል የሚደረገው የሸገር ደርቢ የቀጥታ ስርጭት እንደሚያገኝ የተረጋገጠ ሲሆን ቀጣዮቹ ሦስት ሣምንታት ( ከ 9ኛ – 11ኛ ) የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደማይኖራቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ዲኤስቲቪ በዘንድሮው የውድድር ዓመት 180 ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ ዕቅድ የያዘ ሲሆን እስከ 8ኛ ሣምንት ድረስ 29 ጨዋታዎችን አስተላልፏል። ከተስተካካዩ የሸገር ደርቢ በኋላ ሠላሳኛ ጨዋታውን የሚያስቆጥረው ተቋሙ ከ 12ኛ እስከ 30ኛ ሣምንት ያሉ 152 ጨዋታዎችን በአጠቃላይም 182 ጨዋታዎችን እንደሚያስተላልፍ ተነግሯል። በዚህም ከላይ የጠቀስናቸው 3 ሣምንታት የቀጥታ ስርጭት ሽፋን የማያገኙ ይሆናል።

በተጨማሪ መረጃ የ11ኛው ሣምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችም በአዳማ ከተማ የመቀጠላቸው ዕድል የሰፋ መሆኑ የተሰማ ሲሆን የመርሐግብር ቀን ሽግሽግም ሊኖር እንደሚችል ተጠቁሟል።