ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | ነጌሌ አርሲ በተከታታይ ነጥብ ጥሏል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው የምድብ ‘ለ’ መሪ ነጌሌ አርሲ ነጥብ ሲጥል ባቱ ከተማ አሸንፏል።

ቀን 8:00 ሰዓት ላይ በተደረገ ጨዋታ ነጌሌ አርሲ ከኦሜድላ ተገናኝቶ ነጥብ ተጋርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄን በመምረጥ የግብ ሙከራ ከማድረግ ይልቅ ወደኋላ አፈግፍገው መጫዎትን ምርጫቸው አድርገዋል።

ብዙም የግብ ሙከራ ባልታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ነጌሌ አርሲ ሁለት አደገኛ ሙከራ በሙሉቀን ተስፋዬ እና በፊት መስመር ተጫዋቻቸው በታምራት  ኢያሱ አማካኝነት ሲያድርጉ ሙሉቀን ተስፋዬ ከመሃል ሜዳ አካባቢ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። እንዲሁም አጥቂው ታምራት ኢያሱ ከመስመር የተሻገረውን ኳሰ በግንባር ገጭቶ ጥሩ ሙከራ አድርጓል።

ኦሜድላ በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት በመሃል ስፍራው ተጫዋች በሀቢብ ከድር አማካኝነት ጥሩ ተንቀሳቅሶ የግብ ሙከራ ቢያደርግም የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ ሳያስመለክተን በ0ለ0 ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሽሎ በመግባት ኳስ ተቆጣጥረው በመጫወት የግብ ሙከራዎችን ያደረጉት ነጌሌ አርሲዎች በ52ኛው ደቂቃ አቤል ፋንታ ከአጥቂው ከታምራት ኢያሱ ጋር በጥምረት ወደፊት በመሄድ ግብ አስቆጥሮ ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏል።

ሆኖም ግን በመሪነት የቆዩት ለ4 ደቂቃ ብቻ ነበር። ነጌሌ አርሲዎች ግብ አስቆጥረው ደስታቸውን ገልፀው መረጋጋት ሳይችሉ ቀርተው በተከላካዮቻቸው መካከል የተሠራውን ስህተት በመጠቀም በ56ኛው ደቂቃ የኦሜድላው ተጫዋች አላዛር ተስፋዬ ኳስና መረብ አገናኝቶ ከምድብ መሪው ቡድን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጡ አስችሏል።

በማስከተል በተደረገው መርሐግብር ግቦች መቆጠር የጀመሩት ገና በሁለተኛው ደቂቃ ነበር። ባቱ ከተማን ከደብረብርሃን ያገናኘው የ10 ሰዓቱ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በባቱ ከተማ በላይነት ሲጠናቀቅ በአንደኛው አጋማሽ አራት ግቦችን አስመልክቶናል።

ጨዋታው ከጀመረ ገና በ2ኛው ደቂቃ  ከዚህ በፊት ባሉ ጨዋታዎች ተቀይሮ በመግባት የጨዋታ ክስተት ሲሆን የነበረው ወንድወሰን በለጠ በራሱ ጥረት ከመሃል ሜዳ የደብረብርሃን ከተማ ተጫዋቾችን አታሎ በማለፍ ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ኳስን በቀላሉ አስቆጥሮ ባቱ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመረጋጋት ኳስ ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ደብረብርሃኖች በ13ኛው ደቂቃ በእርስ በርስ ቅብብሎሽ በእስጢፋኖስ ግርማ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። ሆኖም ግን የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከቱት ባቱ ከተማዎች በ27ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ግብ ወንድወሰን በግንባር ገጭቶ አስቆጥሮ ድጋሚ 2ለ1 መምራት ችለዋል።

እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ ዮናታን አምባዬ ከመሃል ሜዳ አካባቢ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ እየገፋ ሄዶ ኳስና መረብ አገናኝቶ 3ለ1 እየመሩ ዕረፍት እንዲወጡ አስችሏል።

እምብዛም የግብ ሙከራዎች ባላስመለከተው በሁለተኛው አጋማሽ ባቱ ከተማ በመከላከል ሲጫወት ደብረብርሃን ከተማ በአንፃሩ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። በዚህ ሂደት ባቱ ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ባስቆጠሯቸው 3 ግቦች 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።