ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ መሪነቱን አጠናክሯል

በምድብ ‘ሀ’ 8ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ጅማ አባ ጅፋር ፣ ስልጤ ወራቤ እና መሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል ።

ረፋድ 3:30 ሲል የጀመረው መርሐግብር ጅማ አባ ጅፋርን ከሞጆ ከተማ አገናኝቷል። በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ከዛ በመቀጠል ጅማ አባ ጅፋር በኳስ ቁጥጥር እና በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ ተሽለው ተገኝተዋል። በአንፃሩ ሞጆ ከተማ የጅማ አባጅፋርን ጠንካራ ማጥቃት ለመቋቋም በከፍተኛ  ጥረት ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በ38ኛው ደቂቃ የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ሙሉዓለም በየነ ግልፅ በሆነ ሁኔታ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳያስቆጥር ማባከን ችሏል። አጋማሹም ያለምንም ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለዐይን ሳቢ እና ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክቶናል። ጅማ አባ ጅፋር የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት ኃይሉን ይበልጥ በመጨመር ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ሞጆ ከተማም በመከላከሉ ረገድ ጥንካሬ ለመጨመር የተጫዋች ቅያሪ አርገዋል። በ63ኛው ደቂቃ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች የሆነው አስቻለው ግርማ ተቀይሮ በመግባት ከመስመር ይዞ በመግባት ኳስን ሰንጥቆ በማቀበል አሚር አብዲ ወደ ግብ ቀይሮታል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሞጆ ከተማ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በ68ኛው ደቂቃ ሞጆ ከተማ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ አሚር ራመቶ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጅማ አባ ጅፋር ግብ ከተቆጠረበት በኋላ የኃይል ሚዛኑን በመውሰድ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። በ81ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋር በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ በመድረስ የመጀመሪያውን ግብ አመቻችቶ ያቀበለው አስቻለው ግርማ ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን ዳግም መሪ ማድረግ ችሏል። በ89ኛው ደቂቃ የሞጆ ከተማው አምበል የሆነው ሲሳይ ሚደቅሳ የመሃል ዳኛውን ውሳኔ በመቃወም በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊዎችን ወደ ሰነጠረዡ አጋማሽ ከፍ ያደረገ ሆኗል።

ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሐግብር የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገው ስልጤ ወራቤ ነቀምት ከተማን አሸንፏል። በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ስልጤ ወራቤ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ነቀምት ከተማ በረጅም ኳስ የፊት መስመር ተጫዋቹን ኢብሳ በፍቃዱን ዒላማ በማድረግ ለሱ ኳስ እንዲደርሰው ሲጥሩ ተመልክተናል። በስልጤ ወራቤ በኩል ጥሩ የኳስ ቁጥጥር በማድረግ የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም አጋማሹ ብዙ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት እና ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ፍላጎት ደካማ የሆነበት አጋማሽ ሆኖ በዚሁ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተጫዋች ቅያሪ ተነቃቅቶ የገባው ስልጤ ወራቤ ተሽሎ ተገኝቷል። ይህንንም ተከትሎ በ53ኛው ደቂቃ ስዩም ደስታ በራሱ ጥረት ተቃራኒ ተጫዋቾችን በማለፍ ግብ አስቆጥሯል። ሁለተኛውን አጋማሽ ቀዝቅዘው ወደ ሜዳ የገቡት ነቀምት ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተነቃቅተው ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም በስልጤ ወራቤ የኋላ መስመር እና ግብ ጠባቂ ጥንካሬ ግብ ሳይቆጠርበት ጨዋታው ተጠናቋል። አዲስ አሰልጣኝ የሾመው ስልጤ ወራቤ ሳይታሰብ በዋንጫ ፉክክር ውስ ጥ የሚገኘው ነቀምቴ ላ ይ ባሳካው ድል ነጥቡን ወደ ስድስት ከፍ በማድረግ ከሰንጠረዡ ግርጌ ቀና ማለት ችሏል።

ቀን 7:30 ላይ በተደረገው ጨዋታ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን ከምድቡ መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጀመረ በ1ኛው ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በቅብብል አብዱላሂ አሊዩ ጋር የደረሰው ኳስ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ ማዳን አቅቶት ግብ አስቆጥሯል። በጊዜ ግብ ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ ጫና ፈጥሮ ተጫውቷል። ይህንን ተከትሎ በ27ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋች የሆነው አቤል ሀብታሙ ከቡድን ጓደኛው የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮታል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው በመጫወት በ36ኛው ደቂቃ ያሬድ ብርሃኑ ለአቤል ሀብታሙ በማቀበል አቤል ሀብታሙ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ አንበል የሆነው ኤፍሬም ገረመው በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቢንያም ካሳሁን አስቆጥሯል። ጨዋታውም በዚሁ በመቀጠል ምንም ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኦሮሚያ ፖሊሶች በተወሰነ መጠን ተጭነው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአንጻሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን አጨዋወት በማበላሸት እና የጨዋታውን ፍጥነት በመቀነስ ጨዋታውን ለማረጋጋት ሲጥሩ ተስተውሏል። ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ያረገውን ጥረት ወደ ግብ መቀየር ተስኖት በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩት ግብ ተጠናቆ ሽንፈት አስተናግዷል። ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ያገኘው ኢትዮ ኤሌክተሪክም ዛሬ ባሳካው ድል ነጥቡን 18 በማድረስ መሪነቱን አጠናክሯል።