ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ የምድቡ መሪ ሆኗል

በምድብ ‘ለ’ ስምንተኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ በግብ ክፍያ በልጦ የምድቡ መሪ መሆን የቻለበትን ውጤት ሲያስመዘግብ ሸገር ከተማ ከመመራት ተነስቶ አሸንፏል።

ቀን 8:00 ሲል በጀመረው የስምንተኛ ሳምንት ሶስተኛ ቀን የመጀመሪያ በሆነው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከፍፁም ጨዋታ የበላይነት ጋር የካ ክፍለከተማን አሸንፏል። በሁለቱም አጋማሽ የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ በኳስ ቁጥጥሩ በልጠው የተገኙት አርባምንጮች ሦስት ግቦችን በአሸናፊ ተገኝ ፣ በእንዳልካቸው መስፍን እና በፍቃዱ መኮንን አማካኝነት በማስቆጠር ነው ማሸነፍ የቻሉት።

ጨዋታው እንደተጀመረ ወደ ተቃራኒ ቡድን ኳስን ይዘው ሲገቡ የተስተዋሉት አርባምንጭ ከተማዎች ገና በ5ኛው ደቂቃ  አህመድ ሁሴን እና በፍቅር ግዛቸው ባደረጉት ቅብብሎሽ ግሩም ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በአንደኛው አጋማሽ ጥሩ እንቅሰቃሴ በማድረግ በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ8ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ወደ ግብ የመታትን ኳስ አሸናፊ ተገኝ በግንባሩ ጨርፎ ወደ ግብነት ቀይሯት 1ለ0 እየመሩ ዕረፍት እንዲወጡ አስችሏል።

አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው  አጋማሽም ውጤቱን ለማስጠበቅ እና ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው በመጫወት የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። ዛሬ ደካማ እንቅሰቃሴ ያደረገው ተጋጣሚው የካ ክፍለከተማ እምብዛም የግብ ሙከራዎችንም ሆነ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም።

65ኛው ደቂቃ ላይ በአሸናፊ ተገኝ ላይ በተሠራው ጥፋት በቀኝ መስመር ያገኙትን የቅጣት ምት እንዳልካቸው መስፍን ቀጥታ ወደግብ በመምታት ኳስና መረብ አገናኝቶ መሪነታቸውን አጠናክሯል። እንዲሁም በ74ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ግብ አስቆጣሪ የሆነውን አሸናፊ ተገኝን ቀይሮ በመግባት ፍቃዱ መኮንን በመጀመሪያ ንክኪው የየካ ክፍለ ከተማ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በአርባምንጭ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሳምንቱ ማሳረጊያ በሆነው በ10 ሰዓቱ መርሐግብር ሸገር ከተማ ከመመራት ተነስቶ ቢሾፍቱ ከተማን አሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ ተሽለው ለመገኘት ጥሩ የኳስ ቁጥጥር ያደረጉት ቢሾፍቱ ከተማዎች በ9ኛው ደቂቃ ዳዊት ሽፈራው በራሱ ጥረት ባስቆጠረው ግብ ጨዋታውን መምራት ችለው ነበር።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተረጋግተው በመጫወት ጫና ሲያሳድሩ የተስተዋሉት ሸገር ከተማዎች ከናፈቃቸው ነጥብ ጋር ለመገናኘት ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ኳስን ገፍተው ወደ ፊት ሲሄዱ በሀይከን ድዋሮ ላይ ጥፋት ተሠርቶ በ37ኛው ደቂቃ ተፈራ አንለይ ወደ ግብ አክርሮ የመታትን ኳስ የቢሾፍቱ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳይቆጣጠራት ቀርቶ ኳሷን ያገኛት ፋሲል አስማማው መረቡ ላይ አሳርፏት 1ለ1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ  ክፍል አምርተዋል።

በሁለኛው አጋማሽ ፍጹም የጨዋታ የበላይነት የወሰዱት ሸገር ከተማዎች በ52ኛው ፣ በ54ኛው እና በ80ኛው ደቂቃ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ግቦች ማሸነፍ ችለዋል። በ52ኛው ደቂቃ አላዛር ሽመልስ የቆመ ኳስ አግኝቶ ወደ ግብ መቷት ተጨርፋ ወደ ግብነት ተቀይራ መሪነቱን ተረክበው 2ለ1 መሆን ችለዋል። መሪነታቸውን ከተነጠቁ በኋላ ቢሾፍቱ ከተማዎች መረጋጋት ተስኗቸው ሲዘናጉ ፋሲል አስማማው ብልጠቱን ተጠቅሞ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸውን አጠናክሯል።

ተጨማሪ ግብ ፍለጋ እስከመጨረሻው ደቂቃ ጫና አሳድረው ሲጫወቱ የተስተዋሉት ሸገር ከተማዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ የመሃል ስፍራ ተጫዋች የሆነው ታሪኩ እሸቱ በራሱ ጥረት ኳስና መረብ አገናኝቶ ሸገር ከተማ 4ለ1 በሆነ ውጤት እሸንፎ እንዲወጣ አስችሏል።