ሪፖርት | ሻሸመኔ እና ባህር ዳር ነጥብ ተጋርተዋል

በሻሸመኔ ከተማ እና በባህር ዳር ከተማ መካከል የተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር 0-0 ተጠናቋል።

ቡድኖቹ በሊጉ የ8ኛ ሳምንት ጨዋታቸው ባደረጉት ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማ ከአዳማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ከተጠቀመው አሰላለፍ ግብ ጠባቂ ላይ አቤል ማሞን አሳርፎ ኬን ሳይዲን ሲተካ ከድሬዳዋ ጨዋታ አንፃር ባህርዳሮች የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። አለልኝ አዘነ እና አባይነህ ፌኖን በፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ሀብታሙ ታደሠ ተክተዋቸዋል።

ቀን 9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ባህር ዳሮች በኳስ ቁጥጥሩ ሙሉ ብልጫ በመውሰድ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ሻሸመኔዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በሚያገኙት ኳስ በጥቂት ንክኪ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ያን ያህል ፈታኝ እንቅስቃሴ ባልተደረገበት አጋማሽ 25ኛው ደቂቃ ላይ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ቻላቸው መንበሩን ከግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ጋር ተጋጭቶ ባስተናገደው ጉዳት ምክንያት አስወጥተው አብዱልቃድር ናስርን ባስገቡት ሻሸመኔዎች በኩል አሸናፊ ጥሩነህ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ወደ ግብ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ የወጣበት ኳስ የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ ነበር።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ለመግባት በተቸገሩት የጣና ሞገዶቹ በኩል 37ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የወሰዱትን ኳስ የአብሥራ ተስፋዬ ከሳጥን አጠገብ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ከቀኝ መስመር ከማዕዘን ከተሻማ እና ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልስበት የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ቸርነት ጉግሳ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራም ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ በድጋሚ ይዞበታል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው ተመሳሳይ በሆነ ሂደት ሲቀጥል የጣና ሞገዶቹ በሚያገኙት ኳሱ ሁሉ በተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 56ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሠ ተከላካዮችን አታልሎ ባመቻቸው ኳስ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ሲይዝበት 60ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሠ በተከላካይ የተመለሰ 62ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ፍሬዘር ካሳ በግብ ጠባቂው የተያዘ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።

ሻሸመኔዎች ከጨዋታ አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥቅጥቅ ብለው በመጫወት እና ጨዋታውንም ለማቀዝቀዝ ሲሞክሩ በተደጋጋሚ ዋና ዳኛው ባሪሶ ባላንጎ ላይ በሚቀርቡ ቅሬታዎች እና በሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች መካከል በሚደረጉ ጉሽሚያዎች ጨዋታው አሰልቺ እየሆነ ሲሄድ 86ኛው ደቂቃ ላይ በሻሸመኔ በኩል ማይክል ኔልሰን በባህር ዳር በኩል ደግሞ ፍሬዘር ካሳ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግደዋል።

 

ከወትሮው በተለየ ጥራት ካለው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተዳክመው የቀረቡት የጣና ሞገዶቹ 88ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ቸርነት ጉግሣ በግራ መስመር በግሩም ሁኔታ እየገፋ የወሰደውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ፍጹም ጥላሁን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ኬን ሳይዲ ይዞበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።