የአሰልጣኞች አስተያየት | ሻሸመኔ ከተማ 0-0 ባህር ዳር ከተማ

“ዛሬ ፍፁም ተፈላሚ ነበርን” አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ

“በየሁለት ደቂቃው እየተኙ የጨዋታውን ስሜት የጨዋታውን ግለት ይገሉት ነበር” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

ሻሸመኔ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ያለ ጎል ካጠናቀቁት ጨዋታ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቃለ ምልልስን አድርገዋል።

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህርዳር ከተማ

ብልጫን ወስደው ማሸነፍ ስላልቻሉት ጨዋታ …

“እግር ኳስ ለተመልካችም አዝናኝ ሆኖ ከማንም በላይ ደግሞ እግር ኳሱ ፖዘቲቭ እግር ኳስ መጫወት ቢቻል በጣም ጥሩ ነበር። ተጋጣሚያችን መርጦት የነበረው የጨዋታ መንገድ በሎው ብሎክ ለመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም መርጦ የተጫወተበት ሁኔታ ነው ያለው ፣ በመጀመሪያም በሁለተኛም አርባ አምስት እኛም ያንን ለማስከፈት ብዙ ጥረት አድርገዋል ልጆቻችን የግብ ዕድሎችንም መፍጠር ተችሏል ፣ ሆኖም ግን ሜዳው ላይ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጉጉት አምክነናቸዋል። ከዛ ውጪ ግን ትንሽ ምቾት የማይሰጥ ለተመልካችም ሜዳው ላይ ለነበረውም እንቅስቃሴ በየሜዳው ክፍል ላይ በየሁለት ደቂቃው እየተኙ የጨዋታውን ስሜት የጨዋታውን ግለት ይገሉት ነበር እና ያ ደግሞ ተጫዋቾቻችን ነርቨስ እንዲሆነ ያደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። እንግዲህ በዕለቱ የነበረውም እንቅስቃሴን ለተመልካች የሚስብ ነው ብዬ አላስብም በየደቂቃው ፊሽካ የሚነፋበት በየደቂቃው ተጫዋቾች እየተኙ የጨዋታውን ቴንፖ የሚያቀዘቅዘበት ሁኔታ ነው የነበረው ለእነርሱ አቻ ነጥቡ አይመስለኝም እጅግ የሚጠቅማቸው ማሸነፍ ይመስለኛል። በእንደዚህ አይነት ደረጃ በእንደዚህ አይነት ውስጥ ሆነህ በይበልጥ ለማሸነፍ መጫወት እና ያንን ሚንታሊቲ እንዲላበሱ ማድረግ የተሻለ ነበር ብዬ አስባለሁ። እነርሱ ከጅምሩም የገቡት የቻሉትን ያህል ችለው ነጥብ ማስጣል እና አንዲት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ነው ከተቻለ ስለዚህ ያሰቡት ተሳክቶላቸዋል ብዬ አስባለሁ በእኛ በኩል ዕርግጥ በጣም የሚያስቆጩ ዕድሎች ባክነዋል ፣ ፍፁም ደግሞ ቴናሊቲ ቸርነት ላይ የተሰሩ ጥፋቶች ዳኛው ሊሰጠን አልቻለም። የእነርሱ ዕይታ ነው እኛ ደግሞ ኮች እዛ ላይን ላይ ቆመን በምንመለከተው እንቅስቃሴ ይገባን ነበር ብለን እናስባለን። ዞሮ ዞሮ አሁን ፊልም በሌለበት ሁኔታ እንዲህ ነው እንዲህ ነው ማለቱ አይጠቅምም ፣ ግን ያንንም ቢሆን ተቆጣጥረን ጨዋታውን አሸንፈን እንለወጣለን የሚል ስሜት ነበር የነበረው በዚህ አጋጣሚ ለተጫዋቾቻችን ትልቅ አክብሮት ነው ያለኝ ማበረታታት ነው የምፈልገው በጣም ትዕግሥትን የሚፈታተን ፍፁም ስሜታዊ የሚያደርግ ጨዋታ ነው የነበረው በየሰዓቱ የሚፈጠሩ አክሽኖች ፣ ያን ከልክ በላይ ያለፈውን ስሜት ተቆጣጥረው ለመጫወት የሄዱበት ርቀት እጅግ ያስደስታል። ሂደቱ ማራቶኑ ረጅም ነው ገና ብዙ ጨዋታዎች ከፊታችን ይጠብቁናል ወደ 21 ጨዋታዎች ስለዚህ በትዕግሥት እያንዳንዱን ጨዋታ መጫወት እንዳለብን ትምህርት ያገኘንበት ነው ብዬ አስባለሁ።”

የተደረጉ ሙከራዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው ማለት ይቻላል ?

“በዛ ደረጃ ነው ለማለት ያስቸግራል ፣ ምክንያቱም ጥራታቸው ከፍ ያለ ቢሆን እንኳን ጎል መቆጠር ነበረበት ብዬ አስባለሁ እና ያ አልሆነም። እንዚህን የበለጠ አሳደገን መምጣት አለብን የሚያጠቃ ቡድን ጋር ስትጫወት ጥሩ ነው ፣ እንደዚህ ደግም ፍፁም ወርዶ መከላከል አንድ ነገር ሆኖ ሳለ በየደቂቃው ደግሞ የጨዋታውን መቆራረጥ እያደረጉ ከጨዋታ ሙድ ለማውጣት የሄዱበት ርቀት ደግሞ እጅግ አሰልቺ ነው። በእንደዚህ ነገር ውስጥ የነበረህን ግለት ቦግ ዕልም እያለ የሚያበላሽ እንቅስቃሴ ስለነበር ተቀብለነዋል ያለውን።”

ማሊያዊው አጥቂ ሱለይማን ትራኦሬ ከክለቡ ጋር ስላለመኖሩ…

“ለዕረፍት እንደሄደ አልተመለሰም አልፏል የዕረፍት ቀኑ አልመጣም።”

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ሻሸመኔ ከተማ

በመከላከሉ ተሽለው በጨዋታው ስለመቅረባቸው…

“ዛሬ ፍፁም ተፈላሚ ነበርን እና ነጥቡ ያስፈልገን እንደነበር ሜዳ ላይ ተጫዋቾች ያሳዩት የነበረው ነገር ጥሩ ነው። ይሄ ስሜት መቀጠል አለበት ነገር ግን ኳስ አጨዋወታችን ላይ ግን የተወሰነ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ ፣ እዛ ላይ ብዙ መስራት እንዳለብን ያሳያል።”

በመከላከሉ ቢሻሉም የግብ ዕድል ግን ስላለመፍጠራቸው…

“ምንድነው ከሽንፈት አስተሳሰብ ቡድኑ መውጣት መቻል አለበት። ሌላው ምንድነው በተቻለ መጠን በየጨዋታው ባዶ እጅ መውጣት ከአሁን በኋላ አያስፈልግም ፣ ቢያንስ አንድ ነጥብ የምንችል ከሆነ ሦስት ነጥብ ካልሆነ ግን አንድ ነጥብ እርሷን አንድ አንድ ነጥብ እየደመርን ሊጉ ላይ ለመቆየት ህይወታችንን ለማርዘም ያለን ዕድል ስለሆነ ያንን ለማድረግ ነው። በቀጣይ በተቻለ መጠን የመከላከል አደረጃጀታችንን ጥብቅ አድርገን በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ከሆነ ጎል ለማግባት እንሄዳለን ፣ ካልሆነ ግን ከጨዋታው ያለችውን አንድ ነጥብ ይዘን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።”

አብዱልቃድር ናስር ተቀይሮ ገብቶ ተቀይሮ ስለ መውጣቱ …

“እንደተጀመረ ገና ደቂቃዎች ሳይሞሉ ያልታሰበ ጉዳት ደረሰብን እና በዛ ነው እርሱን ያስገባነው የነበረው የመስመር ተከላካይ ነው እኛ የመስመር አጥቂ ያደረግነው ስለዚህ ብዙ ለፍቶ ስለነበረ የሆነ የድካም ስሜት አየን ፣ ሁለተኛ ደግሞ በዛ ደቂቃ ላይ በተቻለ መጠን ፉዓድ ፈጠን ያለ ልጅ ስለሆነ በመልሶ ማጥቃት ኳሶች ካገኘን ያንን ለመጠቀም ስንል ፉዓድን አስገብተነዋል።”

ኃይል የበዛበት እና ቀይ ካርዶችም ስለ ነበሩበት ጨዋታ እና ስለ ዳኝነቱ…

“እዚህ ላይ ማውራት አልፈልግም ግን ብቡ ጊዜ ከታች ደረጃህ የሆነ ቡድን ስትሆን በተቻለ መጠን ከታች የሚመጡ ዳኞች ስለሚያጫውቱ ትንሽ ጨዋታው ከብዶት ነበር ዳኛው ይሄንን ነው ማለት የምፈልገው በዳኝነቱ በኩል።”

ስለ ዛሬዋ አንድ ነጥብ ትርጉም…

“ለእኛ ብዙ ነው። ሦስት ነጥብ ምን ያህል እንደሚያሳድገን እናውቃለን ነገር ግን ቢያንስ ባህርዳር ለሊጉ ፌቨራይት ከሆኑ ክለቦች አንዱ ዕርሱ ነው የተጫዋቾች ጥራት ብቻ ሳይሆን ቆይታም አላቸው ፣ ቢያንስ ይሄ ቡድን የሦስት ዓመት ቡድን ነው ስለዚህ ለሊጉ ሻምፒዮንነት የሚጫወት ቡድን ነውና ቢቻል ከዚህ ቡድን አንድ ነጥብ ይዞ መውጣት ለእኛ ትልቅ ነገር ነው። ጨዋታው ላይ ከነበረው ነገር አንፃር ጥሩ ውጤት ነው ማለት ይቻላል።”